Fana: At a Speed of Life!

በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ አዲስ የዲዛይን ክፍተት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ አዲስ የዲዛይን ክፍተት መገኘቱ ተገለፀ።

የቦይንግ ኩባንያ እና የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍ.ኤ.ኤ) በትናንትናው እለት እንዳረጋገጡት በ737 ማክስ አውሮፕላን ዲዛይን ላይ የተገኘው አዲስ ክፍተት የኤሌክትሪክ ሽቦ መቀራረብ ችግር እንደሆነ አረጋግጠዋል።

የቦይንግ ቃል አቀባይ ጎርዶን ጆንድሮ  “ጉዳዩ የቦይንግ አስቸጋሪ ሂደት አካል ቢሆንም፤ ተገቢውን ትንተና ለማከናወን ከአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ጋር በጋራ እየሰራን ነው፤ አሁን የተገኘው ክፍተት የዲዛይን ለውጥ ለማድረግ ያስገድዳል የሚያስብል ደረጃ ላይ ግን አልደረሰም”ብለዋል።

የቦይንግ አውሮፕላን ላይ የተገኘው አዲሱ የዲዛይን ክፍተት የሁለት ሽቦዎች በጣም መቀራረብ መሆኑን በመግለጽ፤ አብራሪዎች ችግሩን ተረድተው በአፋጣኝ ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋን ሊያስከትል ይችላል” ሲል የኒው ዮርክ ታይምስ አስነብቧል።

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በሰጠው መግለጫ፥ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ ሊደረግ በታቀደው የዲዛይን ማሻሻያ ዙሪያ ኤጀንሲው እና የቦይንግ ኩባንያ የተለያዩ ግኝቶችን እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።

ኤጀንሲው አክሎም “በዚህ ሂደት ወቅት ተለይተው የሚታወቁ የደህንነት ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይደረጋል ” ሲልም አስታውቋል።

ቦይንግ በአሁኑ ጊዜ ተቀራርበዋል የተባሉ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን ለመለየት እና  ስህተቱን ተከትሎ የሚደርሰውን አደጋ በተመለከተ ሰፋ ያለ ትንተና እየሰራ መሆኑን አንድ የኩባንያው ባለስልጣን አስረድተዋል።

ቦይንግ በአምስት ወራት ውስጥ በሁለት አደጋዎች 346 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ የማክስ 737 አውሮፕላን ማምረት ማቆሙ ይታወሳል።

 

ምንጭ፡- ሲጂቲኤን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.