Fana: At a Speed of Life!

በ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እየተገነባ የሚገኘው የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ግንባታ ከ43 በመቶ በላይ ደርሷል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ግንባታ 43 ነጥብ 4 በመቶ ላይ መድረሱ ተገለፀ።
የአፍሪካ ብሎም የጥቁር ህዝቦች ነፃነትን የሚዘክረው የአድዋ ሙዚየም ባለ አራት ወለል እና 11 ብሎኮችን የሚይዝ ህንፃ ነው።
ፕሮጀክቱ 1 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ፓርኪንግ፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የመዝናኛ ቦታዎችን ጨምሮ ዋናው የፕሮጀክቱ አካል የሆነውን የአድዋ ሙዚየም ይይዛል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ምሬሳ ሊክሳ ያለምንም እረፍት ስራው 24 ሰአት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የአድዋን ድል ከዚህ ቀደም ከነበረው ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያግዘው ይህ ሙዚየም ጀግኖች አባቶች ከመጀመሪያው ለትግል ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ድሉን ሲቀዳጁ ብሎም የነበሩ ታሪካዊ ተሳትፎዎች የሚዘከሩበት ነው።
የሙዚየሙን ግንባታ በሁለት ዓመት ውስጥ ማለትም በፈረንጆቹ 2021 መስከረም ወር ላይ ለማጠናቅቅ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
ይህ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ኢንጅነር ምሬሳ ተናግረዋል።
የአድዋ ሙዚየም በተለይም በድህረ ኮቪድ ከሚጎበኙ ሀገራት ተርታ ለተቀመጠችው ኢትዮጵያ እንዲሁም አዲስ አበባ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል ።
አሁን ላይ በግንባታ ሂደቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው በላይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ምሬሳ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ 3 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለልማት ተብሎ ለ 20 አመት ታጥሮ በነበረ ስፍራ ላይ ነው እየተገነባ የሚገኘው።
የቻይናው ቻንሲ ስራ ተቋራጭ ግንባታውን እያከናወነ ሲሆን በአማካሪነት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲዛይን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እየተሳተፈ ይገኛል።
በዙፋን ካሳሁን

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.