Fana: At a Speed of Life!

በምርጫው ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰሩ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሃፓ)፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ሆነው ለመቅረብ ዘርፈ ብዙ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የህብረተሰቡን ህይወት ማሻሻል የሚያስችሉ አማራጭ ፖሊሲዎችን ከመቅረጽ ባለፈ ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡
የህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሃፓ) ሊቀመንበር አቶ ቴዎድሮስ ዘርፉ ፓርቲያቸው ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመሪያዎች በመከተል እና ህጋዊ መስፈርቶችን በማሟላት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢሃፓ ዋና የትግል መስመር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ÷ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥም የማህበረሰቡን ህይወት ሊያሻሽል የሚችል እና ዜጎችን ከችግር አረንቋ ሊያላቅቅ የሚችል አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ ይዘን እንቀርባለን ነው የሚሉት፡፡
የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሰረታዊ ችግር ገዠውን ፓርቲ በመቃወም ላይ ያጠነጠነ የፖለቲካ ሂደት መከተል መሆኑን በመጥቀስም፥ በቀጣይ ፓርቲዎች መሰል ችግሮችን በማስወገድ መራጩን የሚመጥን አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ኢንጂነር ጌታነህ ባልቻ በበኩላቸው÷ ባልደራስ በመጭው ምርጫ ለመሳተፍ መወዳደሪያ ፕሮግራሞችን ከማዘጋጀት ባለፈ ሌሎች መሰረታዊ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የባልደራስ መነሻ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥያቄ መፍታት ነው የሚሉት ኢንጂነር ጌታነህ ÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመሳተፍም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት ከተካሄዱት የይስሙላ ምርጫዎች መማር እንዳለበት የሚናገሩት ኢንጂነር ጌታነህ÷ ገዢው ፓርቲም የህዝብን ድምፅ እና ይሁንታ ለማክበር ከወዲሁ ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባው አውስተዋል።
በሌላ በኩል ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማህበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ አማራጭ ፖሊሲዎችን ማቅረብ እንዳለባቸው ነው የሚገልጹት፡፡
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንብር አቶ ግርማ በቀለ ÷ ፓርቲያቸው አሁን ላይ የምርጫ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት እጩዎች የሚተዳደሩበት የምርጫ ስነ ምግባር ሰነድ በማርቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህብር ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እነዚህ ፖሊሲዎችም ከውጭ የመጡ አስተሳሰቦች ሳይሆኑ ከማህበረሰቡ ማህበራዊ ግንኙነት እና አኗኗር የሚመነጩ እንዲሁም ሀገር በቀል እሴቶችን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.