Fana: At a Speed of Life!

ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር ሊሻሻል ይገባዋል – ኢሰመኮ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ በርካታ ድንጋጌዎች ከሰብአዊ መብቶች ሕግና መርሆዎች አንጻር ሊሻሻሉ እንደሚገባ ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪን ለመያዝ፣ ለብርበራ እና በልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴ ኃይል ሊጠቀም የሚችለው፤ ጥንቃቄ የማድረግን፣ የሕጋዊነትን፣ የጥብቅ አስፈላጊነትን፣ የተመጣጣኝነትን እና አድልዎ ያለማድረግን መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እና ሌላ አማራጭ መንገድ የሌለ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን፤ በዚህ ረገድ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥነ ሥርዓት በግልጽ ሊደነገግ የሚገባ መሆኑን፣

በወንጀል የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው የቃል አቀባበል ሂደትን ጨምሮ በማቆያ ቤት ወይም በእስር ወቅት ኢሰብአዊ አያያዝ እንዳይፈጸምበት እና ተፈጽሞም ሲገኝ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ሊካተቱ እንደሚገባ፡፡

ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በእስር በመያዝ፣ በምርመራ፣ በክስ እንዲሁም ምስክርነት በመስጠት ሂደት ሰብአዊ መብቶቻቸውን፣ ክብራቸውና ልዩ ፍላጎቶቻቸውን የበለጠ ሊያስከበሩ የሚያስችሉ ማሻሻያዎች መካተት እንዳለባቸው፡፡

ሕፃናት ከእናታቸው ጋር የሚታሰሩበትን ሁኔታ ለማስቀረት ነፍሰ ጡር ለሆነች ሴት ወይም ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆነ ሕጻን ወይም የምንትንከባከበው የአካል ጉዳተኛ ልጅ ላላት እናት የዋስትና መብት ወዲያውኑ እንዲፈቀድ እና በጥፋተኝነት ፍርድ ጊዜም ከእስር ውጪ ያለ ቅጣት በአማራጭነት እንዲወሰድ፡፡

ማንኛውም የታሰረ ሰው በተጠረጠረበት ወይም በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ሊጣልበት የሚችለውን የመጨረሻውን የእስር ቅጣት እርከን ያክል በእስር የቆየ እንደሆነ ወዲያውኑ ሊለቀቅ እንደሚገባ፡፡

ለሕገ ወጥ መያዝ ወይም ለእስር የተዳረገ ሰው ካሳ የሚያገኝበት ሥነ ሥርዓት ሊደነገግ የሚገባ መሆኑን በሚመለከቱ ማሻሻየዎች ሊደረጉ ይገባል ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት በአጠቃላይ ከ30 በላይ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ የማሻሻያ ምክረ ሃሳብ ከእነ ማብራሪያዎቹ ያቀረበ ሲሆን ለምክር ቤቱ ሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ቀርቧል።

በሌላ በኩል የወንጀል ምርመራ ዓላማ እውነትን ማውጣት መሆኑን፣ መካሄድና መጠናቀቅ ያለበትም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ተጠርጣሪው ሳይያዝ መሆኑን በግልጽ መደንገጉ፣ በስህተት የተሰጠ ፍርድ እንደገና የሚመረመርበት ሥነ ሥርዓት መደንገጉ ረቂቅ ህጉ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር ያሉት ጠንካራ ጎኖች መሆናቸውን ጠቅሷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ “ረቂቅ ሕጉ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም በኮሚሽኑ ሪፖርት የተመለከቱትን የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች በማካተት ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎች ጋር የተጣጣመ ሕግ ማውጣት የግድ አስፈላጊ ነው” ማለታቸውን ከኢሰመኮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.