የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ዛሆ ዢዩዓን ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

January 14, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ዛሆ ዢዩዓን ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው የኮቪድ19 ወረርሽኝ ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ በተለይም በክልሉ ያሉ አዳዲስ ክስተቶችን በሚመለከት መክረዋል፡፡

አቶ ደመቀ የጃክ ማ ፋውንዴሽንን ጨምሮ የቻይና መንግስት እና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን ኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመዋጋት ላደረገችው ጥረት ላደረጉት ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልፀዋል ፡፡

አያይዘውም ቻይና ለኢትዮጵያ አንዳንድ ፕሮጀክቶች የሰጠችው የብድር እፎይታ ጊዜ፥ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19ኝ ተፅዕኖን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቻይና ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በመከተል በህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋምም አድንቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ በውይይቱ ወቅት መንግስት በትግራይ ክልል ስለወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ያብራሩ ሲሆን፥ ዘመቻው በስኬት መጠናቀቁን በመጥቀስ መንግስት በዘመቻው ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየሰራ መሆኑንና በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ዛሆ ዢዩዓን በበኩላቸው በኮቪድ19 አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በአጋርነት በመቆሟ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሃገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!