Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መለያየት የጠፋበት፣ መከፋፈል የተወገደበት፣ የአንድነት በዓል ነው።

ሰውና እግዚአብሔር፣ ምድርና ሰማይ፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሰውና መላእክት አንድ የሆኑበት በዓል ነው። ይህንን በዓል የምናከብረውም መከፋፈልንና መለያየትን በማጥፋት መሆን አለበት። ሰውን ተፈጥሯዊ ልዩነቶች አይለያዩትም። ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ለሰው ልጆች ከፈጣሪ የተሰጡት ጌጦች ናቸውና። የጾታ፣ የቀለም፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ ልዩነቶች የፈጣሪን ድንቅ ጥበብ የሚመሰክሩ ጸጋዎቻችን ናቸው።

ፈጣሪ ተፈጥሮን ያጸናት በልዩነቶች ውስጥ በሚኖር መስተጋብር ነው። ተፈጥሮ ኅብራዊ ሆና በቢሊየኖች በሚቆጠሩ ልዩነቶች ውስጥ የምትኖር ናት። እነዚህ ልዩነቶች ግን በየራሳቸው ለብቻቸው ለመቆም አይችሉም። ከሌላው ጋር መስተጋብር መሥርተው ይኖራሉ። ብቸኝነትና አንድ ዓይነትነት የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ያጠፋቸዋል። ኅብራዊ መስተጋብር ደግሞ የተፈጥሮን ህልውና ያስቀጥላል። ተፈጥሮ በልዩነትና በአንድነት መካከል የሚኖረውን ወርቃማ አማካይ ታውቀዋለች። የህልውናዋ መሠረትም እርሱ ነው።
ተፈጥሮ ፈጽማ ተነጣጥላ፣ መነጣጠል በሚያመጣው መገፋፋት እርስ በርሷ እንዳትጠፋፋ መስተጋብራዊ አንድነቷ ይጠብቃታል።

ተፈጥሮ በመሳሳብና በመዋዋጥ በሚመጣ አንድ ዓይነትነት እንዳትጠፋ ተፈጥሯዊ ልዩ ልዩነቷ ይታደጋታል። ልዩ ልዩነቷ አንድነቷን እንዳይበታትነው፤ አንድነቷም ልዩልዩነቷን እንዳይጠቀልለው ተፈጥሮ ወርቃማውን አማካይ ጠብቃ ትኖራለች። የልደት በዓል ይሄንን ወርቃማ አማካይ የምናስታውስበት በዓል ነው። በልደት በዓል ሰውና አምላክ፣ እንስሳትና ሰው፣ እረኛና ንጉሥ፣ ሴቶችና ወንዶች፣ ሕጻንና አረጋዊ፣ በአንድ በረት ተገናኝተዋል።

እነዚህ ሁሉ በበረቷ ውስጥ ሲገናኙ ሰላምን፣ ይቅርታንና ፍቅርን መሠረት አድርገው ነው። ጠላትነት ጠፍቶ፣ መለያየት ተወግዶ፣ መወቃቀስ ተደምስሶ፣ ቅያሜ ተሠርዞ ነው። ሁሉም በበረቷ አንድ ሆነው በመገናኘታቸው ታሪክ ሠሩ፤ ከበሩ፤ የዘለዓለማዊ ክብር ተካፋዮችም ሆኑ። ኢትዮጵያ የክብር በረታችን ናት። የተለያዩ ማኅረሰቦች፣ አስተሳሰቦች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ታሪኮች፣ ቋንቋዎች፣ ዕውቀቶች፣ ለሚበልጥ ክብር ሲሉ የተሰባሰቡባት በረታቸው ናት። እረኞች፣ ነገሥታት፣ አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ወደ በረቷ ከመጡ በኋላ ከበፊቱ ክብራቸው የሚበልጥ ክብር አግኝተዋል። የሚበልጥ ታሪክ ሠርተዋል፤ በማንነታቸው ላይ ሌላም ማንነት ደርበዋል፤ማንነታቸውን ይዘው በክርስቶስ አንድ ሆነዋል። ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት።

በኢትዮጵያ በረት ውስጥ ያሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሁሉ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን የአንድነት ክብር ደርበዋል። ይህ ክብር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ላለፉት፣ ኢትዮጵያንም ለመሠረቱት ብሔሮችና ብሔረሰቦች ብቻ የሚሰጥ ክብር ነው። በነበራቸው ማንነት ላይ የሚደርቡት ማንነት፣ በነበራቸውም ክብር ላይ የሚደርቡት የላቀ ክብር ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደ ቤተልሔሟ በረት መለያየት፣ መከፋፈል፣ መጠላላትና መቀያየም የሚጠፋባት፣ ሕዝቦቿ አንድ ሆነው ታሪክ የሚሠሩባት ናት። ይህን አንድነት ለመበተንና አዲስ ጠላትነትን ለመትከል የሚጥሩ የሄሮድስ ቢጤዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። የበረቷ ብርሃን ያስጨንቃቸዋል፤ የበረቷ ክብር ያስፈራቸዋል፤ የበረቷ አንድነት ይቆረቁራቸዋል፤ የበረቷ ፍቅር ሰላም ይነሣቸዋል።

ይሄን ልዩ ፍቅር፣ ይሄንን አንድነት፣ ይሄንን ሰላምና ፍቅር ለመተናኮል ሄሮድሳውያን ሰይፋቸውን ያነሣሉ። ክርስቶስንም፣ ድንግል ማርያምንም፣ ዮሴፍንም፣ ሰሎሜንም፣ እረኞችንም፣ የጥበብ ሰዎችንም አያገኟቸውም። ሰይፋቸው የሚያርፈው ምንም በማያውቁ የቤተልሔም ሕጻናት ላይ ነው።

ሐዲሳን ሄሮድሳውያንም በአካልና በወሬ የሚሠነዝሩት ሰይፍ የሚጎዳው በአካልና በአእምሮ ሕጻናት የሆኑትን ነው። የሚያልቁትና እያለቁ ያሉት ሕጻናቱ ናቸው፤ አድገን፣ ተምረን፣ ወላጆቻችንን እንረዳለን፤ ለሀገር ለወገን እንተርፋለን ብለው የሚጓጉት ሕጻናትና ወጣቶች ናቸው እየተጎዱ ያሉት።

ሄሮድሳውያን ደግሞ ለልጆች አያዝኑም፤ ሄሮድስ ምንም ያህል ሰይፍ ቢመዝ፣ ምንም ያህል ሕጻናትን ቢጎዳ፣ ምንም ያህል ለጊዜው ችግር ቢፈጥርም፤ የክርስቶስን ተልዕኮና ጉዞ ግን አልገታውም። ሄሮድስ ክፉ ታሪኩን ትቶ ጠፋ፤ ክርስቶስ ግን የዓለም ብርሃን ነው።

የቤተ ልሔሙ ብርሃን ለዓለም ተርፏል፤ የቤተልሔሙ ፍቅርና አንድነት ለዓለም ተርፏል፤ የቤተልሔሙ ሰላምና ይቅርታ ለዓለም ተርፏል፤ ሄሮድስ ግን የለም።
ለዚህ ነው ሄሮድስነትና ከሄሮድስ ጋር መቆም ከጊዜያዊ ትርፍ ያለፈ ነገር አያስገኝም የምንለው። የበረቱ ዜጎች መሆን ጊዜያዊውን ፈተና የሚሻገር የላቀ ክብር አለው ብለን የምናምነው። በቤተልሔም የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመታት የተፈጸመውን አስደናቂ ታሪክ ለማሰብ ዛሬም ብዙዎች በየዓመቱ ሚሊየኖች ወደ ቤተልሔም ይጎርፋሉ።

በኅብረ ብሔራዊነት ያገኘናቸውን ጸጋዎች ይዘን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ካጸናን፤ ልዩነት መለያየት፣ አንድነት መጠፋፋት አለመሆኑን ካስመሰከርን፣ ሄሮድሳውያንን ተሻግረን ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ እንሠራለን። ሚሊየኖችም ይህንን ታሪክ ለማየት እንደ ቤተልሔም ወደ ኢትዮጵያችን የሚጎርፉበት ዘመን ሩቅ አይሆንም።

መልካም የልደት (የገና) በዓል ይሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.