የሀገር ውስጥ ዜና

በሐዋሳ ከተማ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ሥራ ገቡ

By Tibebu Kebede

January 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐዋሳ ከተማ ባለፉት 6 ወራት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 22 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸውን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እና በመስኩ ያጋጠሙ ችግሮችን የሚገመግም የምክክር መድረክ በሐዋሳ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የከተማዋ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ተሾመ እንዳሉት፥ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ የገቡባቸው መስኮች ግብርና፣ ማምረቻው ዘርፍ፣ አገልግሎት እና ግንባታ ናቸው።

ከ2 ቢሊየን 400 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ሥራ የገቡት ባለሀብቶች ከ3 ሺህ ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

በከተማዋ ያለው ሰላማዊ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው ባለሀብት ወደ ሥራ ለማስገባት ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በከተማዋ ያለውን የባለሀብቶች እንቅስቃሴ በመገምገም የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው ቦታ በመረከብ ወደ ሥራ ያልገቡ 120 ባለሀብቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋልም ነው ያሉት፡፡

የተሰጣቸውን መሬት ሳያለሙ አጥረው በማስቀመጥ ለሌላ ያከራዩ መኖራቸውንም ጠቁመው፥ በ6 ወራት ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠላቸውም ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!