በኢራን የጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን ቀብር ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የ35 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢራን የጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን ቀብር ላይ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ በትንሹ የ35 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።
የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን ባሳለፍነው ሳምንት በኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ መገደላቸው ይታወሳል።
በዛሬው እለትም ጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን ቀብር የነበረ ሲሆን፥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢራናውያንም በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ለመታደም ወጥተው ነበር።
በጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን የትውልድ ከተማ በሆነችው ከርማን ከተማ ሲካሄድ በነበረው የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥም በትንሹ የ35 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።
በተጨማሪም 48 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱንም ነው ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያመላከቱት።
ይህንን ተከትሎም የጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን ቀብር ለሌላ ጊዜ ለመተላለፍ የተገደደ መሆኑን እና ጊዜውም የሚገለፅ መሆኑን ተገልጿል።
ጀኔራል ቃሲም ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውን የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ባሳለፍነው ታህሳስ 24 ማስታወቁ ይታወሳል።
ፔንታገን ጥቃቱ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ የተፈጸመ ስለመሆኑም በጊዜው ገልጿል።
መስሪያ ቤቱ እርምጃው በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የአሜሪካ መከላከያ አባላትን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ተወስዷልም ነው ያለው።
ሆኖም ግን የጄነራል ቃሲም ሱለይማኒን መገደልን ተከትሎ በኢራቅና አሜሪካ መካከል እንደ አዲስ ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል።
ምንጭ፦ www.bbc.com