Fana: At a Speed of Life!

ለጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አቀባበል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ አፍሪካ መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቀባበል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የደቡብ አፍሪካ መንግስት ገለፀ።

በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳት ሲሪል ራማፖሳ ግብዣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥር 2 እና 3 2012 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያካሂዱ ይታወቃል።

በዚህም መሠረት የአቀባበልና ተያያዥ ስራዎች ቅድመ ዝግጅት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፥ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል አስፈላጊውን ሁሉ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራና አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያምን ያካተተ ቡድን በትናንትናው ዕለት ከጆሐንስበርግ ከተማ ከንቲባ ጄኦፍ ማክሁቦ ጋር ተገናኝቶ የተወያየ ሲሆን፥ ከንቲባው የጆሐንስበርግ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል ተዘጋጅታለች ብለዋል።

ጥር 3 2012 ዓ.ም በኢምፔሪያል ዋንደረርስ ስታዲየም በሚኖረው የዳያስፖራ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው በዝግጅቱ ለሚታደመው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መልዕክት እንደሚያስተላልፉም ተናግረዋል ከንቲባው።

በተመሳሳይ ቡድኑ በዛሬው ዕለት በደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝቶ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የአቀባበል ዝግጅትን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

በዚህም በዴቡብ አፍሪካ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ትሴላኒ ሞኩዌና፥ የደቡብ አፍሪካ መንግስት የክብር እንግዳውን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ማረጋገጣቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.