የሀገር ውስጥ ዜና

በ2.1 ቢሊየን ብር የሚገነባው የዋቤ ድልድይ -አጋርፋ -አሊ ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት ተጎበኘ

By Tibebu Kebede

January 24, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሌና የአርሲ ዞንን በማገናኘት ከማዕከላዊ የሀገራችን ክፍል ጋር የሚያስተሳስረው የዋቤ ድልድይ -አጋርፋ -አሊ ከተማ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በመስክ የስራ ቅኘት ተጎበኘ።

በአካባቢው በተካሄደው የመስክ የስራ ቅኘት መርሃ-ግብር ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ እንዲሁም የተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የዞኑና የክልል አመራሮችም ታድመዋል ፡፡

ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ያለበትን ሁኔታን የሚዳስስ ገለጻም ለስራ ሀላፊዎቹ ተደርጎላቸዋል።

56 ነጥብ 6 ኪሎሜትር የሚረዝመው ይህ ፕሮጀክት አሁናዊ አፈጻጻሙ 44 ከመቶ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው እና 180 ሜትር የሚረዝመው የዋቤ ወንዝ ዘመናዊ የድልድይ የቅድመ ግንባታ ስራዎችም እየተፋጠኑ ነው ተብሏል።

የስራ ሀላፊዎቹ በዛሬው የመስክ ቅኝታቸው ከአካባቢው ነዋሪዎችና የመስተዳድር አካላት ጋርም ውይይት አካሂደዋል።

የዋቤ ድልድይ- አጋርፋ- አሊ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሀገራዊ ከፍተኛ አምራች አካባቢዎችን የባሌና የአርሲ ዞኖችን ከማእከላዊ የኢትዮጵያ ክፍል ጋር የሚያቆራኘ በመሆኑ ለአምራች ሸማቹ ሚናው የላቀ እንደሆነ የተቋማቱ የስራ ሀላፊዎች ገልጸዋል።

በቀጣይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ፕሮጀክቱ በተያዘለት መርሃ -ግብር እንዲጠናቀቅ አቅጣጫንም አስቀምጠዋል።

የዚህ ፕሮጀክት ወጪ 2.1 ቢሊየን ብር ሲሆን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፈነውም በኢትዮጵያ መንግስት ነው።

ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ”CCCC” ሲሆን ”Hong – IK Engineering” እና ልደት አማካሪ ድርጅት ደግሞ የቁጥጥርና የማማከር ስራውን እየሰሩ መሆኑን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!