Fana: At a Speed of Life!

ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የዌት ብሉና ፕክል ቆዳዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ታክስ ተነሳ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ለውጭ ገበያ በሚቀርቡት የዌት ብሉና ፕክል ቆዳዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ታክስ መነሳቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ገበያ ያለቀለት ቆዳ ፍላጎት በመቀነሱ ምክንያት በቆዳ ዘርፍ የኤክስፖርት ንግድ መዳከም እንደሚስተዋል ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የዌት ብሉና ፕክል ቆዳ ክምችትና ብክነት መከሰቱ ተገልጿል።

እነዚህን ችግሮች ለማስወገድም የዌት ብሉና ፕክል የበግ፣ የፍየልና የበሬ ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው የኤክስፖርት ቀረጥ ሙሉ በሙሉ መነሳቱን ሚኒስቴሩ አስታወቋል፡፡

በዚህም በፒክልና በዌትብሉ የበግ፣ የፍየል እና የበሬ ቆዳ ላይ ተጥሎ የነበረው 50 በመቶ ታክስ መነሳቱን ነው ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡

የቆዳ እና ሌጦ አቅራቢዎች 30 በመቶ የሚሆነውን ቆዳ ለሃገር ውስጥ አምራቾች የሚያቀርቡበት እና 70 በመቶ የሚሆነውን ቆዳ በፒክል፣ በዌት ብሉ እና በክረስት መልኩ ለውጭ ገበያ እንዲልኩ የሚያስችል መመሪያ መውጣቱም ነው የተነገረው፡፡

ይህም የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት፣ የሀገር ውስጥ የዌት ብሉና ፕክል ከብክነት ለመታደግ እና ከዘርፉ መንግስት ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ እና የዘርፉን ባለሀብቶች የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች አምራቾች ማህበር በበኩሉ መመሪያው እየወደቀ ያለውን የቆዳውን ኢንዱስትሪ የሚታደግ መሆኑን ገልጿል፡፡

የግሉ ዘርፉ እና መንግስት ተቀራርቦ መስራታቸው ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ማሳያ ነው ያለው ማህበሩ 80 በመቶ የሚሆኑ የቆዳ እና ሌጦ አቅራቢዎች ከዘርፉ መውጣታቸውን አስታውሷል፡፡
መመሪያው ወደ ዘርፉ እንዲመለሱ እድል የሚሰጥ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡

በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረስ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አለመሻሻል፣ ለዘርፉ ልማት በመንግስት የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን ማነስ የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ሆነው መቆየታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተካ ገብረኢየሱስ ገልጸዋል፡፡

ይህ ውሳኔ አስከተላለፈበት ጊዜ ድረስ ካለቀለት ወይም እሴት ከተጨመረበት (በአግባቡ የተለፋ፣ የለሰለሰና የተቀለመና ለምርት ዝግጁ የሆነ) ቆዳ በቀር ከፊል ያለቀለትና ጥሬ ቆዳ ወደ ውጭ መላክ በታክስ አማካይነት ክልከላ ተደርጎበት ቆይቷል፡፡

በሃይማኖት እያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.