የሀገር ውስጥ ዜና

በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 22 የሚቆይ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ለልጃ ገረዶች መስጠት ተጀመረ

By Tibebu Kebede

January 25, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 22 ቀን 2013 የሚቆይ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ለልጃ ገረዶች መስጠት መጀመሩን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በዚህም በአዲስ አበባ ከ49 ሺህ በላይ ልጃ ገረዶች በትምህርት ቤቶች እና በጤና ተቋማት የሚሰጠውን ክትባት ያገኛሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁሉተኛ ደረጃ የሚገኝ ህመም ሲሆን በየዓመቱ ከ7 ሺህ በላይ ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እንደሚታይባቸው የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዩሐንስ ጫላ ገልፀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺህ የሚሆኑት በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ተጠቁሟል።

በሽታውን አስከፊ ያደረገው 80 በመቶ የሚሆነው ከ10 እስከ 20 ዓመት ድረስ ምልክት ሳያሳይ ቆይቶ የሚከሰት በመሆኑ ነው ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል።

በሽታው ሂውማን ፓፒሎማ በተሰኘ ቫይረስ የሚመጣ ሲሆን ዋነኛ መተላለፊያው የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው።

ክትባቱን የሚወስዱት 14 ዓመት የሞላቸው ልጃ ገረድ ሴቶች ናቸው።

በፈትያ አብደላ