Fana: At a Speed of Life!

የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር የሚተገበር እንጂ በፍጥነት የሚገባበት አይደለም- መንግስት 

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም /አይ ኤም ኤፍ/ ለኢትዮጵያ የሶስት አመታት ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚሆን የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድርን ሲያጸድቅ ባወጣው መግለጫ ላይ ገንዘቡ ኢትዮጵያ ወደ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ተመን ለምታደርገው ሽግግር አጋዥ ነው የሚለው ከጠቀሳቸው አምስት የሚሆኑ ይዘቶች ውስጥ አንዱ ነው።

አሁን ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የምንዛሬ ገበያ ሀገሪቱ ካላት የንግድ ሸሪክ ሀገራት መገበያያ ጋር የብር ምንዛሬ የሚተመነው ብሄራዊ ባንክ በየእለቱ በሚያወጣው ዋጋ ነው።

በቀጣይ ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ስርአትን ትከተላለች የሚለው ነገር ሲሰማ ተለዋዋጭ የምንዛሬ ተመን ደግሞ በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ገበያ መር የምንዛሬ ተመን አይነት እንደመሆኑ ስለ ጉዳዩ ብዙ ሲባል ተሰምቷል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትሸጠው የምታስገባው በእጅጉ እንደመብለጡ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ ሲወሰን ደግሞ ዛሬ ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የሚያስፈልገው ብር ከቀን ወደ ቀን ስለሚጨምር የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል የሚል ስጋትን መፍጠሩ አልቀረም።

የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል የዚህ ስጋት ተጋሪ ናቸው። አይ ኤም ኤፍ ባወጣው ገለጻ ላይ “ፍሎት” ያደርጋል እንደሚል አንስተው፥ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአንድ ዶላር ዋጋ ላይ የታየውን የ2 ብር ጭማሪ ከዚሁ ጋር አያይዘውታል።

ይህ እየቀጠለ ከሄደ የጥቁር ገበያውም ይጨምራል የሚሉት አማካሪው፥ ሁለቱም ተያይዞ ከወጡ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ነው የሚያስረዱት። የኑሮ ውድነትና ግሽበት ሊያመጣ እንደሚችል በመጠቆም።

አሁን ባለው ሁኔታ ከ20 በመቶ በላይ ከሆነ ብር እየተዳከመ እና ነዳጅ እየተወደደ እንደሚሄድም ይገልፃሉ፥ ምክንያቱም ሲሉ በፈረንጆቹ 2018 17 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያህል የሚያወጣ እቃ ሀገሪቱ ከውጭ  ማስገባቷን እና ይህ የሚመጣ እቃ በዚያ ሁሉ ጨመረ እንደማለት መሆኑን በማስረዳት።

ኢትዮጵያ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር ያገኘችበት ስምምነት ከመጠናቀቁ በፊት ህዳር ወር ላይ ሶስት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ የብር የውጭ የምንዛሬ ተመን በየእለቱ ባልተለመደ መልኩ እየተዳከመ የአንድ የአሜሪካ ዶላር የባንኮች መግዣ ላይ በየእለቱ በአማካይ ከ10 ሳንቲም በላይ ጭማሬ እየታየ፤ የአንድ የአሜሪካ ዶላር የባንኮች መግዣ ጥቅምት ወር ላይ ከነበረበት 29 ብር ከ50 ሳንቲም አካባቢ ህዳር ወር ሳይጠናቀቅ ከ31 ብር በላይ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም በአንድ ዶላር የመግዣ ዋጋ ላይ ይህ አይነት ልዩነት ለመምጣት አመታት ይወስድ የነበረ ቢሆንም የአሁኑ ግን በጥቂት ሳምንታት የታየ ነው።

ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ከአመታት ወዲህ ከተመዘገበው የበለጠ የዋጋ ግሽበት ከተመዘገበበት ወቅት ጋር መገጣጠሙ “እውነት መንግስት ብርን የማዳከሙ ነገር ላይ ጠንክሮ እየሰራ ነው? የምንዛሬ ተመኑንስ በገበያ እንዲወሰን እያደረገው ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን አጭሯል።

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝን ለመሆኑ ከውጭ ምንዛሬ ተመን ጋር በተያያዘ መንግስት ምንድነው ያሰበው ስንል ጠይቀናቸዋል።

እሳቸው የውጭ ምንዛሬ ተመንን አስመልክቶ መንግስት ከሀገሪቱ የጥቅል ወይንም የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር ጋር አጣምሮ የሚሄድበት እንጂ በተናጠል የሚታይ አይደለም ብለውናል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ምላሽ አይ ኤም ኤፍ መግለጫውን ማውጣቱን ተከትሎ ብርን በአንድ ጊዜ ከንግድ ሸሪኮች መገበያያ አንፃር የምንዛሪ አቅሙን በማዳከም ወደ እንደነዚህ አይነት እብደት በፍፁም መግባት አይታሰብም ነው ያሉት።

መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ችግር  ለማስተካክል ሙሉ በሆነ መንገድ በወጪ ንግዱ ላይ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል። የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልም የዚህ አንድ አካል መሆኑን ነው ያስረዱት።

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ በዚህ መንገድም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚተገበርባቸው ሶስት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይኖራታል ብለዋል።

ቅድሚያ ግን አቅርቦትና ፍላጎትን በማቀራረብ የሚኬድበት እንጂ እንደ ከዚህ በፊቱ ብርን በአንዴ በማዳከም አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

አቅርቦቱና ማኔጅመንቱ እየተስካከለ ሲመጣ በራሱ ጊዜ ዋጋውም እየተስተካከለ ይመጣል ያሉት ዶክተር ኢዮብ፥ ነገር ግን በፊት ይደረግ የነበረውን በአንድ ጊዜ ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች አንፃር የብርን አቅም በማዳከም ወይም በፍጥነት ገበያው እንዲወስነው ወደ ማድረግ አይገባም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በ2003 አ.ም ከ20 በመቶ በላይ በ2010 አ.ም ደግሞ በ15 በመቶ ብርን ከውጭ የንግድ ሸሪክ ሀገራት የመገባያያ ገንዘብ አንጻር አዳክሟል።

መንግስት ይህን ያደረገው ምርት ላኪዎች የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን ሲዳከም ለሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ በብር የሚያገኙት ገንዘብ መጠኑ ስለሚጨምር ይበረታታሉ፤ በዚህ ሂደት ውስጥም የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪ ሆነው ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ይጨምራል በሚል ነበር።

ነገር ግን ወደ ውጭ የሚላክ በቂ ምርት እና ተወዳዳሪ ጥራት በሌለበት የተተገበሩ የተመን ለውጦች በመሆናቸው በሁለቱም ጊዜያት ገቢ እቃዎችን በእጅጉ በማስወደድ የዋጋ ንረትን ከመፍጠር የተሻለ ነገር ማስመዝገብ አልተቻለም።

እንደውም በ2010 አ.ም የተደረገው የምንዛሬ ተመን ከዋጋ ግሽበት ባለፈ በባንኮች እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት ጭራሽ ባልተለመደ ሁኔታ አስፍቶታል።

በወጪ ንግዱ ላይ ያሉ ችግሮች እና እንደ የዋጋ ግሽበት ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ተፈትተው የምንዛሬ ተመን በገበያ ከተመራ የሚመከር መሆኑን ሙያተኞች ያነሳሉ።

ዶክተር እዮብ በዚህ ጊዜ የብር የምንዛሬ ተመን አሁን ባለው የጥቁር ገበያ እና የባንኮች ምንዛሬ መካከል ላይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ብለውናል።

ብዙ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ብር ከሌሎች ሀገራት መገበያያ አንጻር ከአቅሙ በላይ ጠንክሯል ይላሉ፤ የምንዛሬ ምጣኔው መስተካከል አለበት የሚሉትም ከዚህ አንጻር ነው።

የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ደግሞ በቂ የሚላክ ምርት በሌለበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ብር ጠነከረ አልጠነከረ ብሎ እርምጃ መውሰድ ተገቢነቱ ሊጤን ይገባል ብለዋል።

አቶ ያሬድ ያሉት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ምርት ላኪዎች ምርቶቻቸውን በህጋዊ ሳይሆን በኮንትሮባንድ ለማስወጣት አዝማሚያ የሚታየው የምንዛሬ ተመኑ የሚያስገኝላቸው ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ ስለሆነም ጭምር ነው የሚሉ አሉ ።

ምክንያቱም ምርትን በህገ ወጥ መንገድ ሸጦ ዶላርን በጥቁር ገበያ መመንዘር አዋጭ የሚሆንበት ሁኔታ ሲፈጠር ታይቷል።

ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ እንደሚሉትም ከዚህ አንጻር በሚላኩ ምርቶች ላይም ቢሆን የምንዛሬ ተመኑን አዋጭ ማድረግ ለሀገር ጠቃሚ ነው ።

የኢትዮጵያ የጥቅል ኢኮኖሚ ችግር ፈትቶ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና ፍላጎትን ማቀራረብ ከተቻለ ጥቁር ገበያ በራሱ ጊዜ ከገበያ ሊወጣ ይችላል ያሉት ዶክተር እዮብ፥ የምንዛሬ ተመን በገበያ ሲወሰን እንደሌሎች ሀገራት የውጭ ምንዛሬ ሱቆች ይኖሩናል ወይ የሚለው ግን ለጊዜው ያልታየ ግን በጥናት የሚመለስ ነው ብለውናል።

በሶስት አመቱ በሚተገበር የኢኮኖሚ ማሻሻያ የምንዛሬ ተመን ላይ ማሻሻያ ማድረግ ብቻውን ግንጥል ጌጥ ሆኖ ሌላ ችግር እንዳይወልድ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን እንዲያሳድግ የሚያደርጉ ቅድሚያ ስራዎች ግን በፍጥነት ይጠበቃሉ ነው የተባለው።

 

 

በካሳዬ  ወልዴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.