የሀገር ውስጥ ዜና

የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ተጀመረ

By Meseret Awoke

January 31, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የአዋሽ ነዳጅ ማቆሪያ የባቡር ሀዲድ ማያያዣና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተጀመረ፡፡

ፕሮጀክቱ የሚገነባው በአፋር ክልል ዞን 3 አዋሽ ሰባት ከተማ ውስጥ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ወጪ 2 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር ሲሆን በአንድ አመት ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የግንባታው ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡

በፕሮጀክቱ የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ መቀሌ የባቡር መስመርን ከአዲስ አበባ፣ ሰበታ ሜኤሶ ደንወሌን የማያያዝ ስራ ይከናወናል፡፡

በፕሮጀክቱ አማካኝነት የአዲስ አበባ ደንወሌ የባቡር መስመርን ከአዋሽ የነዳጅ ማቆሪያ ጋር የማያያዝና የነዳጅ ማራገፊያ መሰረተ ልማቶችን የመገንባት ስራም ይከናወናል፡፡

በተጨማሪም የባቡር መተላለፊያ ፌርማታ ግንባታ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የመተላለፊያ ፌርማታው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት የሚያገለግል ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አሰሪ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሆን የፕሮጀክቱ ተቋራጭ ደግሞ የቻይና ሲቭል ኢንጅነሪግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አማካሪ ደግሞ የቻይና ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪግ ኮንሰልታት ኮርፖሬሽን እንደሆነ ተገልጿል።

በግንባታ ፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የተቋራጩ የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅና ወደ ስራ ሲገባ ከቻይና የተገዙ 110 የነዳጅ ጫኝ ዋገኖች በባቡር መስመሩ አገልግሎት በመስጠት የነዳጅ ጫኝ ቦቴ መኪናዎችን አገልግሎት ይተካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል።

በዋገኖቹ አገልግሎቱን መስጠት ከጊዜ፣ ከወጪና ከቀልጣፋ አሰራር አንጻር የተሻለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ኢዜአ ዘግቧል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!