ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ያገለግላል – የምጣኔ ሃብት ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆናቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ ፈተናዎች መፍትሄን ያስቀመጠ ስለመሆኑ የጠቀሱት ምሁራኑ፥ ዘላቂ የእድገት መሰረቶችን በመጣል የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንደሚያግዝም ያነሳሉ።
የአሰራር ስርዓቱ አለመዘመን፣ የቢዝነስ ከባቢው ምቹ አለመሆን፣ ውስብስብ የአሰራር ሂደት፥ አቅም ያለው የሃገር ውስጥ ባለሀብት እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ የሃገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ችግር ሆኖ መቆየቱን ዶክተር አጥላው አለሙ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ነጻ ገበያ በተባለባቸው ያለፉት አመታት ጎታች የሆኑ ህጎችና አሰራሮች ድንበር ተሻጋሪና ተወዳዳሪ የሀገር ውስጥ ድርጅት እንዳይፈጠር አድርጓልም ነው ያሉት።
ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፥ የግሉ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ላይ ደካማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሃገር ውስጥ ባለሃብቱን በስፋት በማሳተፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ይሆን ዘንድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ወደ ሀገሪቱ ገበያ ከሚገቡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በሽርክና የመስራት አጋጣሚም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትሩፋት መሆኑንም አንስተዋል።
አያይዘውም ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እና የእዳ ጫና መቀነስ እንዲሁም የወጪ እና ገቢ ንግድን ሚዛን ማስጠበቅ ይችላልም ብለዋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ባለሃብቱን ለአመታት ወደ ኋላ የጎተተውን አሰራር እንደሚያዘምንለት ያስረዳሉ።
ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የተገኘው የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር በኢኮኖሚው ውስጥ ፈሰስ ሲደረግ ባለሃብቱን ከፋይናንስ ምንጭ ችግር እንደሚያላቅቀውም አውስተዋል።
ዶክተር አጥላው አለሙ ደግሞ መንግስት ከንግድ ፍቃድ ማውጣት አንስቶ የመሬት አሰጣጥ እና መሰል የድጋፍ ስራዎች ላይ ህግን የማሻሻል እርምጃ ሊወስድ ይገባል ባይ ናቸው።
የዘርፉ ምሁራን ባለሃብቶቹ የገበያ አድማሳቸውን እና ምርታማነታቸውን ከጥራት ጋር በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሰብ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባለሃብቱ ከጊዜያዊ ትርፍ ወጥቶ ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ባላቸው የሀገር ሃብቶች ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በሃይለእየሱስ መኮንን