ማላዊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማላዊ ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን መስክ ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።
የማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንሲስ ካሳሊያ በኬንያ ከኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ አምባሳደር መለስ ዓለም በማላዊ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለማቅረብ መምጣታቸው በኢትዮጵያና በማላዊ መካከል ያለውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክር ጠቅሰው፥ በቀጣይ ማላዊ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት ገልጸዋል።
አዲስ አበባ የሁሉም አፍሪካዊ ቤት ናት ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቀጠናው ሰላም እንዲመጣ እያደረጉት ያለውን ጥረት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው ወዳጅነቱ በንግድ፣ አቪዬሽን እና የግብርና መስኮች እንዲጠናከር የኢትዮጵያም ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶች በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ የሚደረጉበትን ሁኔታ ሀገራቱ ማመቻቸት ይገባቸዋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሰባት ቀን ወደ ማላዊ እንደሚበርና ከማላዊ አየር መንገድ ጋር በስራቲጂካዊ አጋርነት መስራቱ የሃገራቱን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረውም ገልጸዋል።
መረጃው በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።