Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ የ305 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) የ305 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን በጣሊያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ እና  ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሆንጉቦ በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡና በገጠራማ አካባቢ የሚገኙ ከ13 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል።

ድጋፉ በገጠራማ አካባቢዎች በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የገንዘብ እና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፎችን በማቅረብ ለድህነት ቅነሳ እና የዜጎችን መፈናቀል ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑ ተነግሯል።

እንዲሁም በገጠር የገንዘብ ተቋማትን አቅም በማሳደግና የገንዘብ አቅርቦት አገልግሎትን በማሻሻል ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን አርሶ አደሮች ፍላጎት ለማሟላት ይውላልም ነው የተባለው።

በተለይም ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፥ አርሶ አደሮች በህብረት ስራዎች እና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ገንዘብ እንዲቆጥቡ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚውልም ተገልጿል።

በተጨማሪም ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ዘመቻዎችን በማድረግ እና ስልጠናዎችን በመስጠት ግንዛቤ ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑም ተመላክቷል።

ምንጭ፦ www.ifad.org

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.