Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን አፀደቀ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባው በዛሬው እለት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ አድርጓል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ከውጪ ጉዳይና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ከህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ ያቀረበለትን የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።

በዚህም የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን እና የህዝቦችን መብትና ደህንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ መዘጋጀቱ ተነግሯል።

እንዲሁም ግለሰቦች የታጠቋቸውን የጦር መሳሪያዎች የህብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ሊውሉ የሚችሉበትን እድል መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው የተዘጋጀው ተብሏል።

በስራ ላይ ባሉ ህጎችና አሰራሮች ያልተፈተሹ ጉዳዮችን በዝርዝር ህግ መደንገግ እና ወጥነት ያለው ስርዓት መፍጠር በማስፈለጉና ሀገሪቱ ያፀደቀቻቸውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማስፈፀምና ዓለም አቀፍ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ስነ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ መዘጋጀቱን ታውቋል።

በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ድንጋጌ ማንኛውም አይነት የጦር መሳሪያ ፣ብዛት ያላቸው
ጉዳት አድራሽ ስለቶችና ተያያዝነት ያላቸውን የመሳሪያው መገልገያዎችን ይመለከታል።

በዚህም ከፍቃድ ውጪ የጦር መሳሪያ፣ የጉዳት ማድረሻ እቃ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ በጦር መሳሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም አይነት መነጽር ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማውጣት፣ መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ማዘዋወር፣ መጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠንና ማስወገድ ክልክል ይሆናል።

በዚህ ረቂቅ አዋጅ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ሴንጢ፣ አስለቃሽ ጭስና ኬሚካሎች ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆነ ሁኔታ መገልገልና በብዛት ይዞ መገኘት ነው ክልከላ የተቀመጠበት።

ፍቃድ በሚሰጣቸው የጦር መሳሪያዎች መለያ ምልክት ያለው ውይም ሊኖረው ይገባል የሚለውም በረቂቅ አዋጁ የተደነገገ ሲሆን፥ ይህም የመሳሪያ አምራች ከሌሎው ደግሞ በተቆጠጣሪ ተቋሙ መለያ እንዲኖረው ይደረጋል።

የጦር መሳሪያ ፍቃድ ያላቸው አካላት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው አከባቢ፣ በምርጫ ቦርድ በተከለከሉ ስፍራዎች፣ በህዝብ መዝናኛና በስፖርት ማዘወተሪያ፣ በትምህርትና ሀይማኖት ተቋማት እና መሰል የህዝብ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይዞ መገኘትን ይከለክላል።

ፍቃድ ማግኘት ክልከላ የተደረገባቸው ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖትና የእምነት ተቋማት፣የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ናቸው። የጠር መሳሪያ ፍቃዱ በአዋጁ የተቀመጠ ሲሆን፥ የጥይት ብዛት በመመሪያ የሚቀመጥ ይሆናል የሚለውም በአዋጁ ተደንግጓል።

ቀደም ብለው የታጠቁት የህብረተሰብ ክፍሎች የታጠቁት የጦር መሳሪያ ያልተከለከለ እስከሆነ ድረስ በእንደ ዓመት የሽግግር ጊዜ ተቆጣጣሪው ተቋም በአከባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ህጋዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ሆኖም በጊዜ ገደቡ ውስጥ ፍቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ በተቆጣጣሪው የሚወረስ ሲሆን፥ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ ለግለሰብ በሁለት ዓመት ለድርጅት ደግሞ በ5 ዓመት መታደስ አለበት ይላል።

ተቆጣጣሪው ተቋም የፌደራል ፖሊስም ብሄራዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስራ ክፍል አደራጅቶ በቴክኖሎጂ በታገዝ ምዝገባውን መከናወን እንዳለበት በዚሁ አዋጅ ላይ ተቀምጧል፤ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ አነስተኛ ወይም ቀላል መሳሪያን ለአንድ ሰው አንድ ብቻ የሚፈቅድ ነው።

ፍቃድ ለማግኘት ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም በኢትዮጵያ የመኖር ፍቃድ ያገኘ፣ የአደንዛዥ እጽ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበትና የአእምሮው ሁኔታ የተስተካከለ እንዲሁም ከአከባቢው የመልካም ስነ ምግባር መገለጫ ማረጋገጫ ማቅረብና መሰል መስፈርቶች ያስቀመጠ ነው።

አዋጁ የወንጀል ተጠያቂነትም ያስቀመጠ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በአዋጁ የተመለከተውን ክልከላና ግዴታ በመተላለፍ የጸና ነፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያዎችን ያስቀመጠ፣ የያዘ፣ ያመረተ፣ ከሀገር ያወጣና ያስገባ መሰል ክልከላዎችን ሲተላለፍ እስከ 3 ዓመትና ጽኑ እስራትና እስከ 10 ሺህ ብር ይቀጣል።

በዚሁ አንቀጽ ላይ የተባሉትን በብዛት የጦር መሳሪያዎችን ይዞ የፈጸመ ሲሆን ደግሞ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራትና እሰከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ይጣልበታል። የወንጀል ተጠያቂነቱ በየደረጃው በዝርዝር ተቀምጧል።

በአዋጁ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት የሚፈቀድ የጦር መሳሪያ አይነትና ብዛት እንዲሆም በክልሎች የሚገኙ የህግ አስከባሪ አካላት ተልኮና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንዲወጣ ተቀምጧል።

የምክር ቤቱም ከውጪ ጉዳይና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ከህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ ያቀረበለትን የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያዩ በኋላ በ2 ተቃውሞ፣ በአራት ድምጸ ተአቅቦ፤ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም በዛሬው እለት የቀረቡለትን የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ እና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ደምጽ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

በኃይለየሱስ ስዩም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.