አሜሪካ ከኢራን ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከቴህራን ጋር ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።
ዋሽንግተን ለፀጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ ከቴህራን ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ኬሊ ክራፍት ሃገራቸው ከኢራን ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ድርድሩ በዓለም አቀፉ ሰላምና ደህንነት ላይ ሊፈጠር የሚችልን አደጋ እና ውጥረትን ለመቀነስ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
በደብዳቤው አሜሪካ የጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒን ግድያ ራስን ለመከላከል የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ጠቅሳለች።
በተመድ የኢራን አምባሳደር መጂድ ታክት ራቫንች በበኩላቸው፥ አሜሪካ ያቀረበችውን የእንደራደር ሃሳብ የማይታመን ነው ብለውታል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ዋሽንግተን በኢራን ላይ ጠንካራ ያለችውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እያጠናከረች ባለበት ወቅት ይህን ሃሳብ ማቅረቧ ተቀባይነት የሌለው ነው።
ኢራን የጄኔራሉን መገደል ተከትሎ ኢራቅ ውስጥ በሚገኙት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ እርምጃ ወስዳለች።
ምንጭ፦ ቢቢሲ