Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢኳቶሪያል ጊኒን የክብር ኒሻን ተሸለሙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢኳቶሪያል ጊኒን የክብር ኒሻን ተሸለሙ።

ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ውስጥ እና ሰላምን ከማስፈን አንጻር በአፍሪካ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተበረከተ መሆኑም ታውቋል።

ከፕሬዚዳንት ቴዎዶር ኦቢያንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት በባሕል እና ቱሪዝም ዘርፍ አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም ተፈራርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀደም ብለው በጊኒ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር መወያየታቸው እና የኮናክሪን ወደብ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታህሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በጊኒ ሪፐብሊክ እንዲሁም በኢኳቶሪያል ጊኒ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከጊኒ ሪፐብሊክ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ጉብኝታቸው በመቀጠል  በደቡብ አፍሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ።

የደቡብ አፍሪካ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸው በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ የሚካሄድ ነው።

በደቡብ አፍሪካ ቆይታቸውም ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

በተጨማሪም በኢምፔሪያል ወንደረርስ ስታዲየም በሚኖረው የዳያስፖራ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉም ነው የሚጠበቀው።

በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.