በሀረሪ ክልል ካሉ ተሿሚዎችና የመንግስት ሠራተኞች ውስጥ 88 በመቶ የሚሆኑት ሀብታቸውን ማስመዝገባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀረሪ ክልል የሚገኙ ከስምንት ሺህ በላይ ተሿሚዎችና የመንግስት ሠራተኞች ሃብታቸውን አሳውቀው ማስመዝገባቸውን የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ሃብታቸውን አሳውቀው በማያስመዘገቡት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።
የሀረሪ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ካሊድ ኑሬ÷ኮሚሽኑ ባለፉት ባለፉት ስድስት ወራት የፀረ ሙስና ትግሉን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በአዋጁ መሰረት የመንግስት ተሿሚዎችንና ሠራተኞችን ሃብታቸውን አሳውቀው እንዲያስመዘግቡ በሰራው ስራ ከስምንት ሺህ አንድ መቶ በላይ የሚሆኑት ሃብታቸውን አሳውቀው ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል።
በሀረሪ ክልል ከአስር ሺህ ስድስት መቶ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ያሉ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ ከ88 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሃብታቸውን ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
ቀሪዎቹ የወሰዱትን ቅፅ ሞልተው በአፋጣኝ ለኮሚሽኑ መመለስ እንደሚኖርባቸውና ሃብታቸውን የማያስመዘግቡ ከሆነ በህጉ መሠረት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርግ ነው አቶ ካሊድ ያስታወቁት።
የሃብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ዋንኛ ዓላማ ህዝብ በመንግስት ላይ ዕምነት እንዲኖረውና የጥቅም ግጭትን ማስቀረት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚያም ባለፈ ተቋማት በግልፅነትና ተጠያቂነት ስራቸውን እንዲያከናውኑና የሙስና ወንጀል ምርመራን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
ኮሚሽኑ በክልሉ ሙስናን የሚጠየፍና የማይሸከም ማህበረሰብ ለመፍጠር ከሃምሳ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ክበባትን በማቋቋም ትምህርትና ስልጠናእየሰጠ መሆኑንና ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በተሾመ ኃይሉ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!