Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪተካ ሁሉም የፖለቲካ ኃይል በሰከነ መንገድ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት እስኪተካ ሁሉም የፖለቲካ ሃይላት በተደራጀ እና በሰከነ መንገድ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አንጋፋዎች ፖለቲከኞች ዶክተር ዲማ ነግዎ እና የኢህአፓ ፓርቲ መሪ ቆንጂት ብርሃኑ ተናገሩ።

ፖለቲከኞች ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በጠንካራ ተቋማት ግንባታ እና ህዝባዊ ድጋፍ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መደገፍ አለበት ብለዋል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህን እድል በጥንቃቄ መጠቀም ካልቻልን ከአሁን በፊት ያለፉንን ወርቃማ እድል ያከሸፍንበት ታሪክ ሊደገም ይችላል የሚል ስጋታቸውን ተናግርዋል።

አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር ዲማ ነግዎ አብዛኛውን እድሜያቸው በፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው ያሳለፉት፤ እርሳቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ከ50 ዓመታት በላይ ያልዘለቀ መሆኑን ተናግርዋል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግን ሁለት ነገሮች የኢትየጵያን ፖለቲካ ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዳይሸጋገር አድርገውታል ባይ ናቸው።

ቀዳሚው በራሱ የፓርቲዎች ምስርታ በትጥቅ ትግል እና በስውር የጠብመንጃ ፖለቲካ መሆኑ ከዴሞክራሲ ጋር ተላትሟል፤ ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ እና የመንግስት ተቋማት የማይለያዩ ሆነው ወጥ አካሄድ መከተሉ ነው ብለዋል።

በዚህ መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቁጥር እየተበራከተ የመራጮችን ድምፅ እንዲበታተን እና መሃል ላይ እንዲዋልል አድርጎታል።

ዶክተር ዲማ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግን ሁለት ወርቃማ እድሎች አልፈውናል ባይ ናቸው፤ ቀዳሚ ያደረጉት የ1966ቱን አብዮት እና የክሽፈት ታሪክ ነው።

ይህ በጠብመንጃ አንጋቾች የተጠለፈው አብዮት መክሸፍ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እያስቆጨ ባለበት ወቅት ፤ሌላ የቁጭት ሌላ የትካዜ ሁነት ደግሞ ተፈጠረ ይላሉ እኒሁ አንጋፋ ፖለቲከኛ፤ ከድህረ ደርግ ወድቀት ማግስት ያለውን አካሄድ በማንሳት።

አሁን ደግሞ ተስፋ የተጣለበት የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ የቀሩትን ሁነት ያነሱት ዶክተር ዲማ፥ ይህኛው አድል በክሽፈት እንዳይመለስም መጠንቀቅ ያሻል ባይ ናቸው።

የእስካሁኖቹ የክሽፈትታሪኮች በገዥ ፓርቲዎች ብቻ አለመሆኑን ለግንዛቤ በማንሳት፤ ሁሉም በጥንቃቄ ሊራመድ ይገባል ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እድሜያቸውን ያሳለፉት አሁንም ዳግም አንጋፈውን የፖለቲካ ፓርቲ ኢህአፓን በመሪነት እያገለገሉት ያሉት ወይዘሮ ቆንጅት ብርሃኑ፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሰከነ መንገድ መራመድ አለበት ባይ ናቸው።

አንጋፋዋ ፖለቲከኛ ቆንጂት፥ የስሜት ፖለቲካ በርካታ ሀገራትን ዋጋ አስከፍሏል በማለት፤ ድህረ 2011 ሊቢያ እና ሶርያን ለአብነት አንስተዋል።

ዶክተር ዲማ ነግዎ የበለፀገች ሀገር ለመመረት ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት  ሊመሰረቱ ይገባል፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የሆኑ የደህንነት እና የመከላከያ ተቋማት ሊገነቡ ይገባል ባይ ናቸው።

ፖለቲከኛዋ ቆንጂት ብርሃኑም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

ሁለቱም አንጋፋ ፖለቲከኞች በአንድ ነገር ይስማማሉ፥ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከማብዛት ይልቅ፤ ሀገሪቱን እና አለም አቀፍ  ሁኔታውን ያገናዘበ ፖሊስ በመንደፍ መሰባሰብ አለባቸው በሚለው።

በስላባት ማናዬ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.