የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ከኢራን በተተኮሰ ሚሳኤል ሳይመታ እንዳልቀረ ተነገረ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴህራን የተከሰከሰው የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ከኢራን በተተኮሰ ሚሳኤል በስህተት ሳይመታ እንዳልቀረ ተነገረ።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አውሮፕላኑ “በተፈጠረ ስህተት በኢራን ሚሳኤል ተመቷል” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፕላኑ “በስህተት በኢራን ሚሳኤል መመታቱን የሚያመላክቱ መረጃዎች ከተለያዩ ምንጮች ደርሰውኛል” ብለዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጠንካራ ምርመራ መደረግ አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን ጊዜው ገና ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የትሩዶን ሃሳብ ሲጋሩ፥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በአውሮፕላን አደጋው ላይ “ጥርጣሬ” እንዳላቸው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሚዲያ አካላት ደግሞ አውሮፕላኑ ከኢራን ለአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በተተኮሰ ሚሳኤል በስህተት ተመቶ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ሲ ቢ ኤስ የተባለው የሚዲያ አውታር ከአውሮፕላኑ መከስከስ አስቀድሞ ሁለት ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን እና እሱን ተከትሎ ፍንዳታ መከሰቱን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል መገኘቱን የአሜሪካ የደህንነት ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤትን እና የዋሽንግተንና የኢራቅ የደህንነት ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረገው የኒውስ ዊክ ዘገባ ደግሞ አውሮፕላኑ በሩሲያ ሰራሹ ቶር ሚሳኤል ተመቶ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ያመላክታል።
ኢራን በበኩሏ የቀረበባትን ውንጀላ አስተባብላለች።
ቴህራን የዛሬ ሳምንት የሃገሪቱ ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ አዛዥ ጀኔራል ቃሲም ሱለይማኒ በአሜሪካ መገደላቸውን ተከትሎ ከዋሽንግተን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብታለች።
ከጄኔራሉ ግድያ በኋላም በኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን፥ ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቃለች።
ምንጭ፦ ቢቢሲ