Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮችንና አንድን ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ የሚያቃርኑ ትርክቶችን ከማንሳት መቆጠብ አለባቸው – ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሃሰተኛ መረጃዎች እና አንድን ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ የሚያቃርኑ ትርክቶችን ከማንሳት መቆጠብ እንዳለባቸው ምሁራን አሳሰቡ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር በእውቀቱ ድረስ እንደሚሉት ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ፖሊሲ እና መርሃግብራቸውን ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነት ፣ ባህል እና አመለካከት ያላቸው ዜጎች መኖሪያ መሆኗን የሚገልጹት ዶክተር በውቀቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠበ አለባቸው ብለዋል፡፡
ማንኛውም ፓርቲ በየትኛው አካባቢ ተንቀሳቅሶ ሃሳቡን የመግለጽ መብት አለው የሚሉት ዶክተር በውቀቱ ይሁን እንጂ የአንድ ህብረተሰብ ይሁንታ ለማግኘት ሌላውን ማህበረሰብ ባልተገባ መልኩ ከመፈረጅ መቆጠብ እንዳለበት ያነሳሉ።
የህግ ጠበቃ እና አማካሪ የሆኑት አቶ ፋሲል ስለሺ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ያዘጋጇቸው ፖሊሲ እና ፕሮግራሞች ላይ በማተኮር ሊሰሩ እንዲሁም ለሚመርጣቸው ማህበረሰብ ይዘውት የመጡትን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ በግልፅ ቋንቋ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ይሄነው ምስራቅም ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ምርጫውን ለማሸነፍ ይዘውት የመጡትን አማራጭ ሃሳብ መሸጥ ላይ ማተኮር አለባቸው ነው የሚሉት፡፡
የሚያስተላለፉት ሃሳብም እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ እንዲሁም የሌላውን መራጭ ስነ ልቦና ውቅር ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ያዘጋጇቸውን የፖሊሲ አማራጮች ያለምንም ገደብ ለመራጮች እንዲያደርሱ ገዢው ፓርቲ እና የምርጫ ቦርድ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ምሁራኑ ጠቁመዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን የፓርቲዎች መተዳዳሪያ ደንብን ባከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ትዊተር https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.