Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ከ6 ሺህ በላይ አርሶና ዓርብቶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ተሻገሩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑና ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አርሶና ዓርብቶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን በኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ፡፡

አርሶ እና ዓርብቶ አደሮቹ በግብርና ማቀነባበር፣ በማምረቻና አገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በሁለት ዙር የኢንቨስትመንት ፈቃድ ላገኙ ከ6 ሺህ ለሚበልጡ የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች በግብርና ቢዝነስና በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ የቢዝነስ አስተዳደር ስልጠና እንደሚሰጥም ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮቹ ከ6 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የቆጠቡና ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

እነዚህ አርሶና አርብቶ አደሮች በተሻሻለው የኢንቨስትመንት ደንብ መሠረት ከሞዴል አርሶና አርብቶ አደርነት ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ስልጠናው በፌደራል የኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ማዕከል፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክና በሌሎች አካላት የጋራ ትብብርና ቅንጅት ይሰጣል ብለዋል።

ለስልጠናው የሚያስፈልገው ወጪ በኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ በኩል እንደሚሸፈን በመጥቀስም፥ ስልጠናው ከመጭው ቅዳሜ ጀምሮ አዳማ፣ ጅማና ባቱን ጨምሮ በተመረጡ ከተሞች ይሰጣል ማለታቸውን ኦ ቢ ኤን ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.