Fana: At a Speed of Life!

የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር የምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተካሄደ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ሀገሪቱ ያላትን የተበታተነ ሀብትና እውቀት በማሰባሰብና በማስተሳሰር የልማትና ብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ሰፊ ዕድል እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሳይንስ፣ በፈጠራ እና በምርምር ስራዎች የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያሟላ፣ ምቹ ፣ በቂ እና በሚፈለገው ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይልና ግብዓት ለማቅረብ እንዲቻል የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና፣ ምርምር፣ እንዲሁም የፈጠራና ቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር ጥራትና አግባብነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፥ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር የሀገሪቱን የእድገትና ብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ቁልፍ እንዳለው አውስተዋል፡፡

አያይዘውም በዘርፉ ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ፣ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር እንዲሁም የምርምር ስርጸትን በማጠናከር ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡

ልምዳቸውን ያካፈሉት የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ ሃገሪቱን ከድህነት ለማውጣትና እድገትና ብልጽግናን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትስስርና ትብብርን በማጠናከር የሀገር ውስጥ አቅምና እውቀትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በሲሳይ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.