Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድልን ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከርና በተግባር በማረጋገጥ ማክበር ይገባል- የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የአድዋ ድልን ህብረብሔራዊ አንድነትን በማጠናከርና በተግባር በማረጋገጥ ማክበር እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

በክልሉ 125ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዛሬው እለት በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት የአድዋ ድል ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት በመትመም በገዘፈ ወኔና ጀግንነት እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያንን ጦር ገጥመው በዘመናት ርዝመት የማይደበዝዝ ደማቅና ህያው ታሪክ የፃፋበት ድል ነው ብለዋል፡፡

አድዋ ድል ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ደማቅ ጀብዱ የፈፀሙበት የጋራ ታሪክ ማረጋገጫ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የዛሬው ትውልድም ከአያት ቅድመ አያቶች ወኔን፣ ጀግንነትንና ፅናትን ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ህብረት መፍጠር ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ድሉን ከማክበርና ከመጠበቅ ባለፈም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን አጎልብቶ ድሉን የታላቁን የህዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ ጀብድ መፈፀም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የዘንድሮው 125ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር በክልሉ ከወትሮው በተለየ መልኩ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የህዝብን አንድነት በሚያጠናክሩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊው አቶ ዲኒ ረመዳን ናቸው፡፡

በበዓሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ እና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች. የሀገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.