Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም አልሚ ባለሃብቶች ተገኝተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክልሉ የኢንቨስትመንት ልማት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ግብርና፣ ማዕድን እና ቱሪዝምን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ሀብት መኖሩን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተገቢው ልክ እየለማ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ካለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ባለፈ ግን በተወሠኑ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚስተዋለው የአሰራር ችግር መቀረፍ እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአሰራር ላይ ችግር በሚፈጥሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ነው ያሉት፡፡

ከባለሃብቶች ጋር በተያያዘም ለልማት የሚሰሩ ባለሃብቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በተቃራኒው መሬት አጥረው የሚቀመጡና ወደ ስራ የማይገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ በእነዚህ ባለሃብቶች ላይ መሬት የመንጠቅና ሌሎች እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ በኢንቨስትመንት መዳረሻ ቦታዎች አካባቢ የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦት ለመፍታትም ከፌደራል መንግስት ጋር እንደሚሰራ አውስተዋል፡፡

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.