የሀገር ውስጥ ዜና

የባቡር ሀዲድ ሲዘርፉ የነበሩ ዘጠኝ ግለሰቦች ተያዙ

By Meseret Awoke

February 21, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳው ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚያገናኘውን ነባሩን የባቡር ሀዲድ መስመር ብረት ሲዘርፉ የነበሩ ዘጠኝ ግለሰቦችን እጅ ከፍጅ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ፤ ግለሰቦቹ በወረዳው ጠዴቾ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ የዘረፉትን የባቡር ሀዲድ ብረት ጭነው ሊጓዙ ሲሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ የሰረቁትን የባቡር ሀዲድ ብረት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-82408 ኢት በሆነ ሲኖትራክ ተሽከርካሪ ጭነው ከአካባቢው ሊሰወሩ ሲሉ ህብረተሰቡ ለፖሊሰ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ተይዘዋል።

ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደምም በቡድን ተደራጅተው ጨለማን ተገን በማድረግ ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ሲያገኛኝ የነበረውን የባቡር ሀዲድ ብረት ብሎን በመፍታትና በመቆራረጥ ሲሸጡ መቆየታቸው የተደረሰባቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ለማቅረብ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ተናግሯል።

ነባሮቹ የባቡር ሀዲድ ብረቶች ለዘረፋ እየተጋለጡ መሆኑን በመረዳት የሚመለከተው አካል ቸል ሳይል አስቸኳይ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

ህብረተሰቡ የሀዲድ ብረቱ የአገርና የህዝብ ሃብት መሆኑን በመረዳት ከጥፋትና ከዘረፋ ሊከላከል እንደሚገባ በመግለጽ ኮማንደር አስቻለው ጥሪ ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!