Fana: At a Speed of Life!

የመተከል ዞን መቀመጫ በሆነችው ግልገል በለስ ከተማ ተጥሎ የነበረው የሠዓት እላፊ ማሻሻያ ተደረገበት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ የዞኑ መቀመጫ በሆነችው ግልገል በለስ ከተማ ተጥሎ የነበረው ሠዓት እላፊ ማሻሻያ ተደረገበት።

በዞኑ ሠላምና ጸጥታ እያስከበረ የሚገኘው የተቀናጀ ግብረ ሀይል ከፍተኛ አመራሮች ከግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት በነዋሪዎች ተወካዮች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል በከተማዋ የተጣለውን የሠዓት እላፊ ገደብ የተመለከተው ይገኝበታል።

የተቀናጀ ግብረ ሀይሉ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተሟላ መልኩ ለማስከበር በከተማዋ ከምሽቱ አንድ ሠዓት ጀምሮ መደበኛ እንቅስቃሴ ተገድቦ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት የሠላምና ጸጥታ ሁኔታው እየተሻሻለ በመሆኑ በከተማዋ እስከ ምሽቱ 3፡00 ሠዓት ድረስ እንቅስቃሴ እንዲኖር በመወሰን ማሻሻያ ተደርጓል።

በሌላ በኩል በከተማዋ የተገኘው አንጻራዊ ሠላም ዘላቂ እንዲሆን ሕዝቡ በየጓሮው ተደብቀው የሚገኙትን ጸረ ሠላም ሃይሎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማጋለጥ እንደሚገባው በውይይቱ አንስተዋል።

በተጨማሪም ከተማዋ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እውቅና ተሰጥቷቸው ሕዝቡን የማቀራረብ ስራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

ይህም ሊሳካ የሚችለው በከተማ መስተዳደሩ በኩል እውቅና ያላቸው የአገር ሽማግሌዎች ሲሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ግልገል በለስ ከተማ ከአገልግሎት መስጫ ከተማነት ባሻገር የቱሪስት መዳረሻ የመሆን ዕድል እንዳላት ተናግረዋል።

“ግልገል በለስ አሁንም ቢሆን ወደ ሕዳሴ ግድብ የሚጓጓዘው የግንባታ እቃ ከጅቡቲ ወደብ ተጓጉዞ በከተማዋ አርፎ ነው የሚሄደው፤ ግድቡ ሲያልቅ ደግሞ የቱሪስቶች መመላለሻ ከተማ ናት” ብለዋል።

በዞኑ ጸጥታ በማስከበር ላይ የሚገኘው ዋና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ የተቀናጀው ግብረ ሃይል በዞኑ ያጋጠሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ያገኙ ዘንድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ተጠቅሞ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአካባቢው ሠላም የማስፈን፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንስቅሴዎችን መልሶ የማስቀጠልና ሕዝቡን የማደራጀት ስራዎች መሰራታቸውንም እንደተናገሩ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.