Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በአውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ በጀርመን የተሰኘ ማህበር ባዘጋጀውና በበይነመረብ በተካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በጀርመን፣ በእንግሊዝና በጣሊያን የሚኖሩ 93 ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳና የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ የተሳተፉ ሲሆን ባለፉት 3 ዓመታት በሃገሪቱ ስለነበረው የለውጥ ጉዞ ስኬቶችና ተግዳሮቶች፣ ስለ ዘንድሮው ምርጫ ዝግጅትና አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚደረገው የሽግግር ጉዞ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በህወሓት አገዛዝ አማካይነት በሃገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን አምባገነን ሥርዓት በመቀልበስ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን የተወሰዱት የፖለቲካ ሪፎርም እርምጃዎች ትልቅ የተስፋ ብርሃን መፈንጠቃችውን በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገልጸዋል፡፡

አክለውም በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የተሻለ የፖለቲካ ምህዳርና በሃገሪቱ እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመትከል የተገኘውን መልካም እድል በዘንድሮው ሃገራዊ ምርጫ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት እንደሚገባና ለዚህም ገዢው ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም መላው ሃገር ወዳድ ህዝብ የሚጠበቅበትን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ዶክተር ቢቂላ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በሁሉም መስፈርቶች ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅና ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ትንሳዔ የመሰረት ድንጋይ የሚጣልበት እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ሃላፊነቱን እንደሚወጣም ጠቅሰዋል።

የታየውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ይዞ ለመቅረብና በዘንድሮው ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ኢዜማ ባለፉት ሁለት አመታት ጠንካራ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ አብራርተዋል፡፡

ኢዜማ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሰከነና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ በርካታ የፖሊሲ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ወደ ምርጫ ዘመቻ እየገባ እንደሚገኝና በተለያዩ ክልሎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የምረጡኝ ቅስቀሳ ማካሄድ እንዲችል መንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ አቶ አንዱዓለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚፈልጉና በሃገር ቤት ስላለው ሁኔታ መረጃ አግኝተው የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ መሰል መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.