Fana: At a Speed of Life!

በቅስቀሳ ዘመቻው የጥላቻ ንግግሮችን በሚያስተላልፉ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እርምጃ እንወስዳለን – ተፎካካሪ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥላቻ ንግግሮችን የሚያስተላልፉ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

እርምጃው ከፓርቲው አባልነት ወይም ደጋፊነት መሰረዝን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጰያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ዝግጅቶች እያደረጉ ይገኛሉ።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እያካሄዱ ሲሆን ዘመቻው እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይቀጥላል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የምርጫ ቅስቀሳው በተቻለ መጠን በመርህ ላይ የተመሰረተና ከስሜታዊነት የጸዳ ሊሆን እንደሚገባ ይስማማሉ።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እያንዳንዱ ፓርቲ ሲመሰረት ለማሳካት ያቀደውን ዓላማ ከግብ ማድረስ የሚችለው ህዝቡ ስለ ፓርቲው በአግባቡ ተረድቶ ድምጹን ሲሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።

ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው የያዙትን ዓላማ እንዲያሳኩ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ የህብረተሰቡን ልዩነት የሚያጎሉና አንድነትን የሚሸረሽሩ ንግግሮችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ፓርቲያቸው በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ እንዲህ አይነት ስህተት እንዳይፈጠር አስቀድሞ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ፓርቲያቸው ለምርጫው በሁሉም ረገድ እያደረገ ያለው ዝግጅት በስነ-ምግባር የተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

“ለዚህ ደግሞ የፓርቲውን የስነ-ምግባር ደንብ በማጽደቅ ደንቡን ለሁሉም ደጋፊዎች ያሰራጨ ሲሆን በመላ አገሪቱም ለደጋፊዎቹ ስልጠና ተሰጥቷል” ብለዋል።

የቁጫ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የድርጅት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ባንድራ በላቸው እና የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግርማ ጫሞ ፓርቲዎቻቸው የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሄዱ የሌሎች ፓርቲዎችንም ሆነ የህብረተሰቡን ክብር በማይነካ መልኩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከምርጫ ቦርድ መመሪያ ባለፈ የየራሳቸውን የቅስቀሳ ነጥቦች አውጥተው ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

ይሁንና ፓርቲዎቹ ካወጡት የስነ ምግባር መመሪያ ውጪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህዝብን ከህዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ የጥላቻ ንግግሮችን በሚያስተላልፉ የፓርቲው አባላትም ሆነ ደጋፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.