Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ በሚያከናውኗቸው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎች መወዳደሪያ ፖሊሲያቸውን ለመራጩ ማሳወቅ ላይ ማተኮር አለባቸው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ በሚያከናውኗቸው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎች መወዳደሪያ ፖሊሲያቸውን ለመራጩ ማሳወቅ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ምሁራን ገለጹ፡፡

ምሁራኑ ዜጎችን ለግጭት የሚያነሳሱ አላስፈላጊ የሀሰት መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችን ከማስተላለፍ መቆጠብ እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፤ መራጮችም ፓርቲዎች ይዘውት የመጡትን አማራጭ ሃሳብ ለመረዳት እና የሚጠቅማቸውን ለመምረጥ የቀረቡ ፖሊሲዎችን በሚገባ መመዘን ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዕጩ ዶክተር አሰግድ ሽመልሽ የተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አካሄድ የሚበረታታ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ቀናት የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብራቸውን በይፋ ያስጀመሩ ፓርቲዎች ትኩረታቸው ምልክቶቻቸውን ማስተዋወቅ ላይ ነበር የሚሉት ዕጩ ዶክተር አሰግድ፤ የቅስቀሳ ዘመቻው ጥሩ መንፈስ ያለው እና ህብረተሰቡንም ስጋት ውስጥ ያልከተተ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ዘመድኩን መካሻ በበኩላቸው፤ የተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ የምርጫ ድባብ ላይ እየገባን መሆኑን በሚያሳይ መልኩ እየተካሄደ ነው ይላሉ፡፡

‘ይሁን እንጂ ከጅምሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ አካላት የምርጫ ዘመቻው መጀመሩን አናውቅም’ በሚል ሰበብ ለሂደቱ እንቅፋት ሲሆኑ መስተዋሉን አንስተዋል፡፡

ዕጩ ዶክተር አሰግድ ፓርቲዎች በቀጣይ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ላይ ፖሊሲዎቻቸውን እና ፕሮግራሞቻቸውን ማሳወቅ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ነው የሚገልጹት፡፡

በአንፃሩ ‘እከሌ መጥፎ ነው’ ከሚል የውንጀላ አስተሳሰብ በመውጣት ‘እኛ የተሻልን ነን’ የሚለውን መሰረታዊ የቅስቀሳ መነሻ እንደ ጽንስ ሃሳብ መውሰድ አለባቸው ይላሉ፡፡

ምርጫ በትንሽ ስህተት ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ጊዜ ነው የሚሉት አቶ ዘመድኩን፤ በቀጣዩ ሂደት ፓርቲዎች ዜጎችን ለግጭት የሚያነሳሱ ሀሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮችን ከማስተላለፍ መቆጠብ አለባቸው ይላሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ለሁሉም አባሎቻቸው ውስጣዊ እና የስነ ምግባር ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት አለባቸው የሚሉት ዶክተር አሰግድ፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸውም ለደጋፊዎቻቸው አርዓያ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ምርጫ ውሳኔ መሆኑን መረዳት አለበት የሚሉት ምሁራኑ፤ ለዚህም የቀረቡ አማራጭ ሃሳቦችን ፈትሾ በመየለት የሚጠቅመውን መምረጥ እንዳለበት ነው የሚገልጹት፡፡

ለዚህም መራጩ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ያቀረባቸውን ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መመዘን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅም ሁሉም ህብረተሰብ የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.