የሀገር ውስጥ ዜና

በድባጤ ወረዳ ሳስ ማንደን ቀበሌ የእርቅ ስነ-ስርዓት ተፈፀመ

By Tibebu Kebede

February 26, 2021

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በድባጤ ወረዳ ሳስ ማንደን ቀበሌ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አብረው ከሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የእርቅ ስነ-ስርዓት ተፈፀመ።

በእርቅ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከጉሙዝ ማህበረሰብ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከሳስ ማንደን ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር በባህላዊ ስነ-ስርዓት የእርቅ ሠላም ተፈፅሟል ።

በእርቅ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉ እና የአጎራባች ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓት እርድ በመፈጸም አጥንት በመስበር በደም በመጨባበጥ ሁለቱንም የማህበረሰብ ክፍሎች የእርቅ ስነ ስርዓት እንዲፈጸም አድርገዋል።

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የእርቅ ስነ-ስርዓቱ የህዝቦችን ወንድማማችነት፣ አብሮነት እና ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን በመግለጽ፣ ህዝቡ በዚህ ወቅት ያጋጠመውን ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣት ከመጠራጠርና ከመከፋፈል ይልቅ አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

የእርቅ ስነ-ስርዓቱን የፈፀሙት ሁለቱም የማህረሰብ ክፍሎች በበኩላቸው መንግሥት ሁለቱን ወገኖች በማገናኘት ለፈፀመው እርቀ-ሠላም በማመስገን፥ በቀጣይ ከመንግሥት ጎን በመሆን የህዝቦችን ሠላምና አንድነት የሚያናጉ የጥፋት ኃይሎች እንደሚታገሉ ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!