Fana: At a Speed of Life!

የባቢሌ ፓርክ ከጉዳት ለመታደግ በሶስት አካላት መካካል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የባቢሌ ፓርክና ዝሆኖችን ከጉዳት ለመታደግ የኢትዮዽያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ የኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ ።

እነዚህ አካላት የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት በፓርኩ ችግሮችና መፍትሄው ዙሪያ ትናንት በጂግጂጋ ከተማ   ከተወያዩ በኋላ ነው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት÷ የስምምነት ሰነድ ተፈርሞ እና ወደ ስራ መግባቱ ፓርኩን ከጉዳት ለመታደግ መሰረታዊ  መፍትሄ ተደርጎ የሚወሰድ  ነው።

በዋናነትም የፓርኩ ሀብት  ህብረተሰቡ የኔ ብሎ እንዲጠብቀው የማድረግና ተጠቃሚ እንዲሆን የማስቻል ስራ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት  አምስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች በፓርኩ የሰፈሩ የህብረተሰበ ክፍሎች መውጣት አለባቸው፣ ሌሎች ተግባራትም በጥናት ላይ ተመስርተው መሰራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት አለባቸው ያሉት  አቶ ሀይለማርያም ፋውንዴሽናቸውም ለዚህ ውጤታማነት በትኩረት  እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ጉዳይ ክላስተር አስተባባሪው አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው÷  በአካባቢው ከለውጡ ወዲህ  ሁለቱ ክልሎች ተቀራርበው ባከናወኗቸው  አበረታች ስራዎች ሰላምን በማስፈን ወደ ልማት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

አያቶቻችን ያወረሱንን ብርቅዬ ሀብት የሆኑትን የባቢሌ ዝሆኖች ተጠብቀው እንዲቆዩና ለዚህም የፓርኩ ወሰን መከበር ይገባዋል ብለዋል።

ፓርኩ የሁለቱም ክልሎች ህዝቦችን ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ በጋራ ለመሰራት  የኦሮሚያ ክልላዊ  መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል።

ከፓርኩ ጋር ተያይዞ ያሉ የአመለካከት እና የግንዛቤ ክፍተቶች ለመቅረፍ ይሰራል ያሉት ደግሞ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ናቸው።

ክልሉ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በልማት ፣ ሰላምና ጸጥታ ላይ የሚያካሄደውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ፓርኩ የተጋረጠበትን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ክልሉ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ያሉትአቶ መስጠፌ የዝሆኖች መጠለያ ፓረኩንም ከጥፋት ለመታደግ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፌደራል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ብርቱ ጥረትን የሚጠይቅ ቢሆንም በቁርጠኝነት በትብብር ከተሰራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።

የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ወደ ተግባር እንዲቀየር በጋራና በባለቤትነት ስሜት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በውይይት መድረኩ የኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች አጎራባች ዞንና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ በ1970ዎቹ ከተቋቋሙት የዱር እንስሳ ጥበቃ ማዕከላት አንዱ ሲሆን  በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች መካከል  6ሺ 982 ሄክታር መሬትን በመሸፈን በውስጡ 320 ዝሆኖች  እንደሚገኙ  ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.