Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ለ53 ወረዳዎች የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ጥናት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ለ53 ወረዳዎች የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት ጥናት መካሄዱ ተገለጸ፡፡

የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከደቡብ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል ጥናትና የአደጋ ስጋት ቅነሳ የተሰራላቸው ወረዳዎች የርክክብ ስነ ስርአት በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሄዷል፡፡

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሁሉንም አካላት የጋራ ጥረት ይጠይቃል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ እርዳታ የመጠየቅን ያህል አስቸጋሪ ነገር የለም፡፡

ከተመጽዋችነት ለመላቀቅ ዋነኛ ተግባር በልማት ስራ ላይ የላቀ ተሳትፎ ማድረግ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የኢኮኖሚ እድገት ሲጨምር የአደጋ ስጋትን መቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ እና የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት በሀገሪቱ ምቹ ስነ ምህዳር እና የተፈጥሮ ሀብት እያለ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ህብረተሰቡን መታደግ ባለመቻሉ ከውጭ የሚለገስ እርዳታ ስንጠብቅ መኖራችንን ጠቁመዋል፡፡

እርዳታ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ሚናው የላቀ ቢሆንም ካለው እምቅ አቅም አንጻር ከተመጽዋችነት መላቀቅ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በ54 ወረዳዎች የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያስጠናው ጥናት በዘርፉ ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ወሳኝ ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.