Fana: At a Speed of Life!

ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ስናይፐር፣ ብሬን፣ ሽጉጥና ከ5 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ጥይቶች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል ከጭነት ጋር ተመሳስሎ በረቀቀ መንገድ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ስናይፐር፣ ብሬን ፣ ሽጉጥ ፣ ከ5 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ ጥይቶች እንደተያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን አስታወቀ፡፡

መነሻውን ጎንደር ያደረገ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ/አ 99483 አይሱዙ ተሽከርካሪ ከጫነው ጭነት ጋር በማመሳሰል 2 ብሬን፣ 2 ስናይፐር፣ 38 ትልቁ እና 25 ትንሹ ኢኮልፒ ሽጉጦች፣ 5 ሺህ 992 የክላሸንኮቭ ጥይት፣ 892 የኢኮልፒ ሽጉጥ ጥይት፣ 5 የስናይፐር ጥይት፣ የብሬን እግር እና ሁለት የብሬን ዝናር የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረገውን ክትትል መሰረት በማድረግ በጉሌሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው መንደር ሰባት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተሽከርካው ላይ ከተፈጨ የፕላስቲክ ምርት ጋር በማመሳሰል የጦር መሳሪያውንና ጥይቶቹን ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ቢሞከርም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል አዲስ አበባ ውስጥ መያዝ እንደተቻለም ነው የገለጸው፡፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያውን ሲያዘዋወሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልፆ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ እየተራቀቀ መምጣቱን ገልጿል፡፡

የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ህገ-ወጥ ተግባር በማጋለጥ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካለት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.