የሀገር ውስጥ ዜና

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በ35 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ

By Tibebu Kebede

March 01, 2021

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀርቡ ወረዳ በ35 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ያስገነባቸውን ስድስት የተለያዩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል መንግስት እንዲሁም የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ፕሮጀክቶቹ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 52 ሺህ 400 ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ዋናው ትኩረታችን ለሕይወት በጣም አስፈላጊ በሆነው በውሃ ላይ ነው ብለዋል። ሁሉም ማህበረሰቦች ንጽህናው የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ከአጋር እና ከባለድርሻ አካላት መስራታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በሀርቡ ወረዳ ከፈረንጆቹ 2007 ጀምሮ 112 ሺህ 450 ዜጎችን የጤና፣ ትምህርት፣ ንጹህ ውሃ እና ምግብ ዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል።

ባለፈው ዓመትም ድርጅቱ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ ፈሰስ በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎችን የመሰረታዊ ጤና እና ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!