የሀገር ውስጥ ዜና

በወጣቱ ላይ የተሰራውን የጥላቻ ትርክት በትምህርት ስርዓት ማስተካከል ይገባል – ብሔራዊ የወጣቶች ምክክር

By Tibebu Kebede

March 01, 2021

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በወጣቱ ላይ የተሰራውን የመለያየትና የጥላቻ ትርክት በትምህርት ስርዓት መመለስ እንደሚገባ ብሔራዊ የወጣቶች ምክክር ጠየቀ።

ይህ የተጠየቀው “በስልጡን ምክክር አዲስ የተስፋ ምዕራፍ” በሚል እየተካሄደ ባለው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ወጣቶች በሃገራቸው ጉዳይ ያደረጉት ብሔራዊ ምክክር በተወካያቸው ወጣት ተሰማ ካሳ በኩል ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ባላቸው የጋራ አጀንዳና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የወጣቶች ደህንነት፣ ስራ አጥነትና የትምህርት ጥራት ውይይቱ ያተኮረባቸው ነጥቦች እንደነበሩ ዘርዝሯል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በትምህርት ስርዓት የተደገፈ የመለያየትና የጥላቻ ትርክት በወጣቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ወጣቶቹ በአጽንኦት ማንሳታቸውን ተወካዩ ገልጿል።

ይህንን ትርክት በማረም የቀና ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ስርዓቱ ያሉ ክፍተቶች መቃኘት እንዳለባቸውም ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

እንደ ወጣት ተሰማ ገለጻ ነጻና ገለልተኛ የትምህርት ተቋማትን በመገንባት ጥራት ያለውና ዘላቂ የትምህርት ስርዓት መገንባት እንደሚቻል ወጣቶቹ በምክክራቸው አመላክተዋል።

የነበሩ ችግሮችን በማረም የተሻለች ኢትዮጵያን በዘላቂነት ለመገንባት እየተሻሻለ ባለው የትምህርት ስርዓት እንዲታይ ወጣቶች በተወካያቸው በኩል ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የተማሪ ተወካዮች ያደረጉትን ውይይት የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ሻሩ ማርቆስ አቅርቧል።

የትምህርት ፖሊሲና ስራ አጥነት፣ የህግ የበላይነትና የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ የውይይታቸው ትኩረት እንደነበሩ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን በምጣኔ ሃብት ልማት የተሻለች የሚያደርጉ ተማሪዎችን ለማፍራት የተቀረጸው የትምህርት ፖሊሲና ስራ አጥነት ትኩረት እንደሚያሻው መጠቆማቸውን አብራርቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!