Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ስፖርት ኮሚሽንን ለመደገፍ እና ስፖርቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀምሯል-  አቶ ዱቤ ጅሎ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ስፖርት ኮሚሽንን ለመደገፍ እና ስፖርቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ ገለፁ።

አቶ ዱቤ ለክልሉ የሚደረገውን ድጋፍ በማስመልከት ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጥተዋል ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም  የጁንታው የህወሓት ቡድን በወሰደው የክህደት እርምጃ  የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገር ሀብትና ጉልበት የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶች ከጥቅም  ውጪ አድርጓል  ፣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉ ይታወሳል ።

በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት ከተጎዱ የመንግስት ተቋማት መካከል የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን  አንዱ መሆኑን ያነሱት አቶ ዱቤ ÷ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ለበርካታ ዓመታት ያፈራቸው ሀብቶች ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች እና የስፖርት ትጥቆች ወድመዋል  ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ቁመዋል ሲሉ ገልጸዋል ።

የትግራይ ክልል በአትሌቲክስ ፣ በእግር ኳስ ፣ በብስክሌት እና በሌሎች ስፖርቶች ሀገራችንን የሚወክሉ እና ውጤታማ ስፖርተኞች መፍለቂያ የነበረ ቢሆንም በተፈጠረው የሰላም ችግር በአሁኑ ሰዓት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን አንስተዋል ።

በመሆኑም የክልሉን ስፖርት ኮሚሽን መልሶ ለማደራጀት እና ለማቋቋም እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴውን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስችል የድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አቶ ዱቤ ገልፀዋል።

የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴውን በዋናነት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት የሚመራ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክን ጨምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሌሎች የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራትን እና  ተጠሪ ተቋማት የተካተቱበት ነው ብለዋል ።

የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽኖችም በዚህ መርሐ ግብር እንደሚሳተፉም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም ታዋቂ አትሌቶች እና አሠልጣኞች ክልሉን ለመደገፍ እና መልሶ ለማቆቋም በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ውይይት ተጀምሯልም ነው ያሉት  ።

የሚደረገው ድጋፍም የገንዘብ እና የአይነት መሆኑንም ነው የገለፁት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ።

በመግለጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕረዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው÷ ለክልሉ ድጋፍ ለማድረግ ሳንሰባሰብ ተግባብተን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል ።

ስለዚህ በገንዘብም ይሁን በቁሳቁስ ክልሉን ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል ።

አቶ ኢሳያስ በክልሉ የሚገኙ በፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦችን እና በሌሎች እግር ኳሳዊ ጉዳዮች ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.