Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ የሚጠቀማቸው የራሱ የዲጂታል ግብዓቶች ስላሉት በአገሪቱ የሳይበር ምህዳር ጥበቃ ውስጥ መካተቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመረጃ ስርዓት ለምርጫው ሂደት የሚጠቀማቸው የራሱ የዲጂታል ግብዓቶች ስላሉት በአገሪቱ የሳይበር ምህዳር ጥበቃ ውስጥ መካተቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በአገራዊው ምርጫ የሚሳተፉ ተቋማት የመረጃ መረብ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

በተቋማቱ ፍላጎት መሰረት ባለሙያ የመመደብ፣ ከስልጠና እስከ ቴክኖሎጂ ፍተሻ  ተግባራትን በማከናወን ምርጫው ያለሳይበር ስጋት እንዲካሄድ ኤጀንሲው ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጿል።

አገሮች በሚያካሂዱት ምርጫ ላይ በተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት ምክንያት ብዙ ጉዳቶችን አስተናግደዋል።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ በምታካሂደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ በሌሎች አገሮች የተከሰተው የሳይበር ጥቃት እንዳይፈፀም ስለተደረገው ቅድመ ዝግጅት ኢዜአ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን አነጋግሯል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመረጃ ስርዓት ለምርጫው ሂደት የሚጠቀማቸው የራሱ የዲጂታል ግብዓቶች ስላሉት በአገሪቱ የሳይበር ምህዳር ጥበቃ ውስጥ መካተቱን አንስተዋል፡፡

የአገሪቱ የሳይበር ምህዳር ቢጠበቅም በምርጫው ላይ ሚና ያላቸው ተቋማት ትክክለኛውን አሰራር ባለመከተላቸውና ብቁ የሰው ኃይል ባለመመደባቸው ምክንያት ራሳቸውን ለሳይበር ጥቃት ሊዳርጉ እንደሚችሉም በመጠቆም አስጠንቅቀዋል።

“የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ይህን ስጋት በመፈተሸ የሚጠቀማቸውን የቴክኖሎጂ ደህንነት አስቀድሞ ማረጋገጥ፣ ብቁና ስነ-ምግባር ያለው የሰው ሃይል መመደብ፣ ውስጣዊ የሳይበር ደህንነት ፍተሻዎችን የማካሄድ ሙሉ ሃላፊነት አለበት” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እንደ አገር በምርጫው ላይ ቀጥተኛ ሚና ያላቸው ተቋማት የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስባቸው በቂ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም 24 ሰዓት በተጠንቀቅ የሚሠራ “የሳይበር ሬዲነስ ቲም” ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ቡድኑ ከዋና ስራው ወጣ ብሎ የሁኔታ ትንታኔዎችን አስቀድሞ እየሰራ ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ የማድረግ አገራዊ ተልዕኮ እንዳለውም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የተለዩ ጥቃት አድራሾች በምርጫው ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የአመራሮችን እና የሌሎችን ተቋማት የመረጃ መረብ ጠልፈው ጉዳት እንዳያስከትሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ዶክተር ሹመቴ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድንና የሌሎች ተቋማትን ውስጣዊ የቴክኖሎጂ አቅም እና የሰው ሃይል ብቃት ለማሳደግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተቋማቱ ፍላጎት መሰረት ባለሙያ የመመደብ፣ ከስልጠና እስከ ቴክኖሎጂ ፍተሻ ተግባራትን በማከናወን ምርጫው ያለሳይበር ስጋት እንዲካሄድ ኤጀንሲው ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ማረጋገጡን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.