Fana: At a Speed of Life!

አምራቾች የድንጋይ ከሰል እጥረት የሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አምራቾች የድንጋይ ከሰል በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ባለማግኘታቸው የሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን ገለፁ፡፡

አምራቾች እንደሚሉት አሁን ላይ 60 በመቶ የሚሆነው የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሃገራት የሚገባ ነው።

ባለፈው አመት ብቻ ኢትዮጵያ ከውጭ ለምታስገባው የድንጋይ ከሰል ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ አውጥታለች።

የድንጋይ ከሰል ማዕድን የሚገኝበት መሬት በማዕድን አውጭዎች ሳይሆን በአካባቢው ወጣቶች መያዙ በቂና ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል እንዳይቀርብ ማድረጉ ተጠቁሟል።

ከማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በሀገሪቱ በጥናት የተለየ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ቢኖርም በዚህ ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ማዕድን አውጭ ኩባንያዎች ስራቸውን አቁመዋል፡፡

የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፥ ችግሩ የአካባቢው ወጣቶች እኛ መስራት አለብን የሚል አቋም በመያዛቸው በተፈጠረ አለመግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል።

የስራ እድል ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም ወጣቶች እና ኢንተርፕራይዞች ከማዕድን አውጭ ኩባንያዎች ጋር መስራት የሚችሉበት እድል ሰፊ እንደነበረም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

ሆኖም የክልል የስራ ሀላፊዎች ይህንን በማመቻቸት በኩል ክፍተት እንደነበረባቸውም ነው የተነገረው።

ሲሚንቶ አምራቾች በበኩላቸው የድንጋይ ከሰል ማዕድን እንዳያወጡ መከልከላቸውን ይናገራሉ፤ ሚኒስትሩ የአምራቾች ቅሬታ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ለማውጣት የተከለከለ የለም ብለዋል።

በዚህ መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ስራዎችን ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከአራት በላይ አምራቾች ፈቃድ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።

በቀጣይም መስፈርቱን አሟልተው ከተገኙ ወደዚህ እንዳይገቡ ከልካይ የለም ብለዋል ሚኒስትሩ።

በኢትዮጵያ በ20 ቦታዎች የድንጋይ ከሰል ማዕድን መኖሩ በጥናት መለየቱ የተገለፀ ሲሆን፥ በኦሮሚያና ደቡብ ክልል ያሉ ኢንተርፕራይዞች ማዕድኑን እያቀረቡ መሆኑ ተጠቁሟል።

በጌታሰው የሽዋስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.