Fana: At a Speed of Life!

”የመደመር መንገድ‘ መጽሐፍ ከሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ ባሻገር ከፍልስፍና እና ፖለቲካ አንፃርም የላቀ ስራ ነው- ደራሲያን እና ምሁራን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ”የመደመር መንገድ‘ መጽሐፍ ከሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ ባሻገር ከፍልስፍና እና ፖለቲካ አንፃርም ላቅ ያለ ስራ ነው ሲሉ ደራሲያን እና ምሁራን ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ÷ ሰባተኛ የህትመት ውጤት የሆነው “የመደመር መንገድ” መጽሐፍ ትናንት ምሽት በአንድነት ፓርክ ተመርቋል።

በመጽሐፉ ምረቃ ስነስርዓት ላይ ደራሲያን እና ምሁራን “የመደመር መንገድ” መጽሀፍ ላይ ያላቸውን አስተያየትና ምልከታ ለታዳሚያን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልሳን መምህሩ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በመጽሐፉ ውስጥ መሪ ሳይሆን ፀሀፊ ነው ያገኘሁት ብለዋል።

መጽሐፉ ፍፁም ገለልተኛ በሆነ መንገድ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚተነትን መሆኑን አክለዋል።

መጽሀፉ የቀረበበት ቅርጽና የቋንቋ አጠቃቀም የላቀ መሆኑን የገለፁት ዶክተር በድሉ÷ መፅሐፉ አተራረኩ፣ የሥነቃል እና ተረት እንዲሁም በአቀራረቡ አጠቃላይ በሥነጽሁፍ ደረጃው ከፍ ያለ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

በውስጡ የያዛቸውን ታሪኮች በቀላል መልኩ የቀረበበት መንገድ ለአንባቢዎች የሚመች መሆኑን ገልፀው÷ በመጽሐፉ በስንኞች እና በመሳጭ  እውነተኛ ታሪኮችም ጭምር የታጀበ መሆኑን አመላክተዋል።

ከትውልድ መንደራቸው በሻሻ አንስቶ እስከ ቤተመንግሥቱ እና ሌሎችም አገራዊ ጉዳዮችን መያዙን አስረድተው ያልጠሩ የሚመስሉ ጉዳዮችን የሚያጠራ በውብ አቀራረብ የቀረበ ጽሑፍ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።

በመጽሀፉ ላይ ምልከታዋን ያስቀመጠችው ደራሲ ህይወት እንሻው በበኩሏ÷ የመጽሀፉን ስነጽሁፋዊ ይዘት ቃኝታለች።

በመጽሀፉ ታሪክ ሳይሰለች መቅረቡ፣ የትረካ ውበት እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀቱ እና አዳዲስ አተሳሰቦችን ይዞ መምጣቱን ገልፃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍን ከህዝብ ጋር እንደ አንድ የመገናኛ ዘዴ በስልጣን አስተዳደር ውስጥ እየታለፈ ያለውን ታሪክ በጽሁፍ መግለፃቸው መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግራለች።

የትረካው ጥዑምነት ምስል ከሳችነት ከባድ ሀሳቦችን በቀላል ትረካ ለማቅረብ መሞከሩን እና የዓላማ ጽናትን በቀላል ትረካ ያስረዳበት መንገድ በስነ ጽሁፋዊ ይዘቱን የላቀ ስራ እንደሚያደርገው ነው የተናገረችው።

የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ”የመደመር መንገድ‘ መጽሐፍን ከፍልስፍና ፖለቲካ እና ስነጽሁፍ አንፃር ተመልክተውታል።

መጽሀፉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መፃፉ በአንባቢውና በደራሲው መካከል የአድማስ ውህደትን የፈጠረ ነው ብለዋል።

መጽሀፉ የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያዊያን መፍታት እንደሚቻል አዲስ ሀሳብ ይዞ የቀረበ ነው በማለት፤ በወጣትነት፣ በሰላም  ትግል እና ይቅርታ እንዲሁም  ሌሎችም  በተዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.