የሀገር ውስጥ ዜና

የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

By Abrham Fekede

March 09, 2021

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ሁለት የቢራ ፋብሪካዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተለያዩ የድጋፍ ማዕቀፎችን ዘርግቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

ሆኖም የማምረቻ ተቋማት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ሲሉ የጥራት የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እሼቴ አስፋው ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በተደረገ ክትትል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገው በተገኙ ሁለት የቢራ ፋብሪካዎች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት የቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት እንደነበረባቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህም የራሳቸውን የትርፍ ህዳግ ለማስፋት ሲሉ እንደፈለጉ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢነት የሌለው እና ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ እሸቴ ሁሉም የማምረቻ ተቋማት እንደዚህ ያለ ተግባር ከመፈጸም መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሰል ስርዓት አልበኝነትን ለመቆጣጠር የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለው መግለጻቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!