የሀገር ውስጥ ዜና

በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ

By Tibebu Kebede

January 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገባ የነበረ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በሰበታ ከተማ ተያዘ።

የሰበታ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያው የተያዘው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው።

የሰበታ ከተማ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል በአይሱዙ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተጭኖ ከቦንጋ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ 52 ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያ መያዙንም ቢሮው አስታውቋል።

ተሽከርካሪው በረቀቀ መንገድ በድብቅ በተዘጋጀ ስፍራ መሳሪያዎችን ጭኖ ሲጓዝ እንደነበር የሰበታ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ፍተሻ የጦር መሳሪያዎቹ መያዛቸውን ጠቅሶ፥ አሁን ላይም በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድቷል።

ፀረ ሰላም ሀይሎች የህዝቡን ሰላም ለማወክ ሌት ተቀን የሚሰሩትን ስራ ለመቆጣጠር የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያለው ፖሊስ መምሪያው፤ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት እንዲያሳውቅም ጥሪውን አቅርቧል።