የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም፥ ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገር እንግዶች እንዲታደሙ እየተሰራ መሆኑን እና ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።
አያይዘውም እንግዶችን በብቃት ለማስተናገድ ዐቢይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች በየዘርፉ ተዋቅረው ሰፊ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ገፅታው ሳይበረዝ እንዲከበር እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅም የጎንደር ከተማና የአካባቢው ሕዝብ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የጥምቀት በዓል በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ይከበራል።