አደጋን አስቀድሞ መተንበይና መከላከል የሚያስችል ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አደጋዎችን አስቀድሞ መተንበይ እና መከላከል በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።
ለአምስት ቀናት የሚቆየውን ውይይት ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ አደጋ ስጋት ቅነሳ (UNDRR) እና ሲ.አይ.ኤም.ኤ የጥናት ፋውንዴሽን ጋር በጋራ ያዘጋጀው ነው።
የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራዎች የአደጋ ፀባይን፣ የአደጋ ተጋላጭነትንና አደጋ የመቋቋም አቅምን በመረዳት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ ይህም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔን ለመስጠት ተገቢ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዕቅዶችና ለማውጣትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመምረጥ እርምጃ ለመውሰድ አብይ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ውይይቱ አደጋን በመቀነስ በሀገሪቱ ለአደጋ የማይጋለጥ ህብረተሰብን ለመፍጠር፣ አሁን ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ፣ የመሬት መሸራተት እና መሰንጠቅ አደጋን የዘላቂ ልማት መርሃ ግብር እና ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አጣምራ መከላከል እንድትችል ልምድ የምታገኝበት መሆኑም ተገልጿል።
እንዲሁም ፖሊሲ እና ስትራቴጅው በእውቀትና ክህሎት የተመሰረት እንዲሆን መድረኩ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የሰንዳይ ፍሬም ወርክን በመተግበር በሀገሪቱ ለአደጋ የማይበገር ህብረተሰብ ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ ይሆናል ተብሎም ታምኖበታል።
በመድረኩ ላይ በመስኩ እውቅናና ከፍተኛ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ልምዳቸውን በማካፈል በአደጋ ስጋት ቅነሳ ትግበራ ላይ ሳይንሳዊና ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀርባሉ።
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ውይይት በዘርፉ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ተመራማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የክልል፣ የአዲስ አበባ እና የተቋሙ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛል።
በፀጋዬ ንጉስ