Fana: At a Speed of Life!

የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና ሊጫወት እና ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን ሊቆም ይገባል – የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና እንዲጫወት እና ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንዲቆም አሳሰበ፡፡

ምክር ቤቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአሜሪካ ተወካይና የመጋቢት ወር ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሊንዳ ግሪኔልድ በጻፈው ደብዳቤ፥ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት መንግስት በህወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እስከሚያጠናቅቅ እና ክልሉ ወደነበረበት እስከሚመለስ ድረስ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ እና ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በደብዳቤው የምክር ቤቱ አባላት ለኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ላሳዩት ትኩረት አድናቆታቸውን ገልጾ፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላምና መረጋጋት ተምሳሌት መሆኗን አንስቷል፡፡

አያይዞም የሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ባለፉት ሶስት አመታት የቀድሞው ስርአት ዘዋሪ በነበረውና ፀረ ዴሞክራሲ በሆነው የህወሓት ቡድን እክል እንደገጠመውና መደፍረሱንም አውስቷል፡፡

ቡድኑ በተደጋጋሚ ያደርጋቸው ከነበሩ የጥፋት እንቅስቃሴዎች ይመለስ ዘንድ የቀረቡለትን የሰላም አማራጮችና ሽምግልና በመግፋትም ወደ ጥፋት ድርጊት መግባቱንም አስታውሷል፡፡

አሁን ላይም ህወሓት ወደ ወንጀለኛ ቡድንነት መቀየሩንና ኢትዮጵያን ወዳለመረጋጋት ለመክተትና ህዝቦቿን ለመጉዳት ገንዘብ መድቦ በመንቀሳቀስ ይህን እኩይ ድርጊቱን ማረጋገጡንም ጠቅሷል፡፡

ቡድኑ ስልጣን ላይ እያለ ከፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል ባለፈ አሁን ላይ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና የተሳሳተ መረጃ በመልቀቅ፥ የኢትዮጵያን መንግስት እና መከላከያ ሰራዊት ስም ለማጠልሸት ብሎም የህዝቡን ስም ለማጉደፍና ጥላሸት ለመቀባት የሚጠቀምበት መንገድ ጊዜ ያለፈበትና አጥፊ አካሄድ መሆኑንም ምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡

ህውሓት ኢትዮጵያውያንን በዘርና በሃይማኖት ከመከፋፈል ባለፈ በሃገሪቱ ላይ በርካታ በደሎችና ወንጀል መፈጸሙን ያነሳው ምክር ቤቱ ፥ ይባስ ብሎም ሃገሪቱ ወደ ብጥብጥ እንድታመራ ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያነሳው፡፡

ቡድኑ ሲፈጽመው ከቆየው ወንጀል ባሻገር ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ማድረሱን እና ይህን ተከትሎም መንግስት ህግን የማስከበርና ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ስራ መስራቱንም አስታውሷል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት አባላትም በተመሳሳይ መልኩ ለሚፈጸም ጥቃት እርምጃ እንደሚወስዱ ያነሳው ምክር ቤቱ፥ የኢትዮጵያ መንግስት አንድነትን እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍ እንደሚገባውም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ከዚህ አንጻርም የፀጥታው ምክር ቤት ህወሓት ሃገሪቱን ወደ ብጥብጥና ትርምስ ለመክተትና የቆየ ህልሙን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዙ አጋሮቹን እና የውጭ ሰርጎ ገብ ሃይሎችን አካሄድ በአንክሮ ቢመለከተው የተሻለ ነው ብሏል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤትም መንግስት ህግና ስርአትን ለማስከበርና በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት ትክክለኛ እና ገንቢ ሚናውን በመጫወት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንደሚቆም ያላቸውን እምነትም ገልጿል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.