Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 75 በመቶዎቹ ሙሉ በሙሉ ስራ ጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ ድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ ማዕከል በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ 75 በመቶዎቹ ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመራቸውን አስታወቀ፡፡

በአባል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተከናወኑ የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ተግባራትን ዝርዝር ሪፖርት ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዚህም ግምገማ የአባል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የየበኩላቸውን የክንውን ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን÷ አገልግሎት ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ ወደ አገልግሎት እየተመለሱ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በጤናው ዘርፍ በክልሉ ከሚገኙ ሆስፒታሎች 75 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን 10 በመቶ የሚሆኑት በግማሽ አቅም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ተመላክቷል።

አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኙ የጤና ተቋማት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ ይገኛሉም ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም 30 የተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት ሰጭ ቡድኖች በየአካባቢው በመዘዋወር የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ በመስጠት ላይ ናቸው።

54 አምቡላንሶች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም ተጨማሪ 52 አምቡላንሶች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉም ነው የተባለው።

በዚሁ ሳምንት አንድ ሺህ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተዘጋጁ የፈተና ጣቢያዎች መውሰዳቸው ተገልጿል።

በክልሉ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ዝግጅት ተጠናቆ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት በቅርቡ መወሰኑም ነው የተገለጸው።

ስለሂደቱም ከመምህራንና ወላጆች ጋር ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን÷ ከዚሁ ጎን ለጎን ለተማሪዎች፣ ወላጆች እና መምህራን የስነልቦና ድጋፍ በባለሙያዎች መስጠት ቀጥሏል።

በተጨማሪም የኮቪድ 19 የማህበረሰብ አቀፍ የምርመራ ዘመቻ በቀጣዩ ሳምንት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁም ነው የተገለጸው።

በግብርናው ዘርፍም ለክልሉ የግብርና መዋቅር ስራ የማስጀመሪያ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተልኳል።

መደበኛ የግብርና ስራን ከመጭው የክረምት ወቅት በፊት ለማስጀመር በርካታ ስራ መሰራቱ የተጠቀሰ ሲሆን፥ በ20 ወረዳዎች የግብርናን መዋቅር ስራን ለማስጀመር የመልሶ ማቋቋም ስራ ተሰርቷል። በ7 ወረዳዎች የመስኖ ስራ ተጀምሯል ነው የተባለው።

የግብርና ስራ ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር የግብዓት አቅርቦት የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የምግብ ስርጭት የተካሄደ ሲሆን የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ባልሆኑ 13 ወረዳዎችም የምግብ አቅርቦት እንዲደርስ ተደርጓል።

ክልሉን የህብረት ስራ ፌዴሬሽን ወደ ስራ በማስገባት ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ የሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት እና ያደረ ግብአት የማቅረብ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገምግሟል ።

የውሃና የንፅህና አገልግሎት በተመለከተም በቀረበው ሪፖርት  በአብዛኛው የውሃ አገልግሎት ተቋማት ስራ የጀመሩ ሲሆን÷ ውሃ ለማህበረሰቡ በቦቴ የማቅረብ ስራ መቀጠሉ ተገልጿል።

በዚህም 162 የውሀ ቦቴዎች ተሰማርተዋል 79 ሺህ ተጠቃሚዎች በቀጥታ ከውሃ ቦቴዎች አገልግሎት እያገኙ ሲሆን ሌሎች ከመደበኛ የውሃ መስመር አገልግሎት እያገኙ  መሆኑ ተመላክቷል።

በክልሉ 13 ውሃና ፍሳሽ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ ከመሆኑም ባለፈ÷ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች መልሰው ስራ እንዲጀምሩ  መደረጉና የውሃ ታንከሮች በየአካባቢው መተከላቸው ተገልጿል።

የፀጥታ እና ፍትህ መዋቅሮች ወደ ሰራ የማስገባት ተግባራት ውጤት ማስገኘት መጀመሩንና አብዛኛው የክልሉ የመደበኛ ፖሊስ አባላት ወደ ስራ መመለሳቸው ተመላክቷል።

በተጨማሪም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ ኣስተዳደር ጋር በመቀናጀት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የዕርዳታ አቅርቦቶችን በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ መቅረቡ ቀጥሏል።

በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እስካሁንም እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ለተባሉ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ ማቅረብ ተችሏል።

በቀጣይም ዜጎችን በቋሚነት መልሶ የማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ የሚያስችል ስራ ለመስራት እቅድ ተዘጋጅቶ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በአትኩሮት እየተከናወነ እንደሚገኝ መገለጹን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.