የሀገር ውስጥ ዜና

ኢንስቲቲዩቱ ኮቪድ19 በማህበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ የመዛመት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ

By Tibebu Kebede

March 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ኮቪድ19 በማህበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ የመዛመት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ኢንስቲቲዩቱ ቫይረሱ ባለፉት ሰባት ቀናት ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሰባት ቀናትም 49 ሺህ 326 ሰዎች ተመርምረው 9 ሺህ 329 ግለሰቦች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ጠቅሶ፥ ይህም ከ100 ግለሰቦች በአማካኝ 19 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያመላክታል ብሏል፡፡

ካለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ32 በመቶ ጨምሯል ያለው ኢንስቲቲዩቱ፥ 121 ግለሰቦች ህይወታቸውን ሲያጡ ካለፉት ሳምንታት አንጻር በ89 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሷል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ወደ ፅኑ ህሙማን ህክምና ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥርም ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ሲሆን፥ ትናንት ብቻ 467 ሰው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉም ነው ያለው፡፡

ወደ ኮቪድ19 የህክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ግለሰቦች ውስጥ 69 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑም ገልጿል፡፡

ከዚህ አንጻርም ማንኛውም ግለሰብ ማስክ ማድረግ፣ የእጅ ንጽህናን በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ተገቢውን የጥንቃቄ መንገድ በመተግበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እንዲከላከል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!